በማዕከላዊ ጎንደር ዞንና በጎንደር ከተማ አስተዳደር የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በድህረ ምርጫው ለሀገር ሰላምና ደኅንነት እንደሚሠሩ አስታወቁ፡፡

0
47

በማዕከላዊ ጎንደር ዞንና በጎንደር ከተማ አስተዳደር የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በድህረ ምርጫው ለሀገር ሰላምና ደኅንነት እንደሚሠሩ አስታወቁ፡፡

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 18/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በጋራ በሰጡት መግለጫ በ6ኛው ሀገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ አሉ የሚሏቸውን ቅሬታዎች በሕግ ብቻ ምላሽ እንዲያገኙ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

6ኛው ሀገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ የራሱን የታሪክ አሻራ ጥሎ አልፏል፡፡ የምርጫ ሂደቱ በሚፈለገው ልክ ትክክለኛ እና ተዓማኒ ሁኖ እንዲያልፍ ብዙ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል ነው ያሉት ፓርቲዎቹ፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና በጎንደር ከተማ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤታቸው በምርጫው ሂደት ላይ ያተኮረ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ከጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ጥምረት በመፍጠር ወሳኝ በሚባሉ ሀገራዊ ጉዳዮችና ምርጫውን ሰላማዊ፣ ትክክለኛና ፍትሐዊ እንዲኾን ሲሠሩ መቆየታቸው በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

በጋራ ምክር ቤቱ ከምርጫው ቀደም ብሎ ሰላምን ለማስጠበቅ የተለያዩ ሥራዎች መሠራታቸውን የገለጸው ምክር ቤቱ በሀገሪቱ በተካሄደው ሕግን የማስከበር ዘመቻ የሚጠበቅበትን ሚና ሲጫወት መቆየቱ ተነስቷል፡፡

ምክር ቤቱ የተለያዩ ችግሮች ሲፈጠሩ በየሳምንቱ በመገናኘት ችግሮችን ለመፍታት እንደተሞከረ አመልክቷል፡፡ በምርጫው ሂደት መራጮች ካርድ እንዲያወጡ እና የቅድመ ምርጫው ሂደት ስኬታማ እንዲኾን ከተለያዩ የመስተዳድር አካላት ጋር በመተባበር ምክር ቤቱ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል፡፡

በምርጫው ሂደት ላይም ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ምርጫው በሰላም እና በሚፈለገው ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት መሠራታቸው በመግለጫው ተነስቷ፡፡

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ የሚያነሱባቸው ጉዳዮች ካሉ በሕግ እንዲታዩና የሀገር ሰላምና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲቀጥል የበኩላቸውን ሚና ለመጫወት በሙሉ ድምጽ መስማማታቸውን በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞንና በጎንደር ከተማ አስተዳድር የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ውስጥ ስምንት ፓርቲዎች መሳተፋቸውን ከምክርቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ዘጋቢ- ፍፁምያለምብርሃን ገብሩ-ከጎንደር

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here