በመስኖ ከዘሩት ስንዴ የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ የሰብል ቁመናቸው እንደሚያሳይ የባንጃ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡

46
ባሕር ዳር:መጋቢት 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በባንጃ ወረዳ በተያዘው በጀት ዓመት ከ 2 ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት በበጋ ስንዴ በዘር ተሸፍኗል፡፡
አርሶ አደር አጋሉ አላምረው በባንጃ ወረዳ ሰንከሳ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶአደር አጋሉ ካሁን በፊት ገብስን ጨምሮ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን ያመርቱ ነበር፡፡ በዚህ ዓመት ከነበረው አሠራር ወጥተው ስንዴ በመስኖ እያመረቱ ነው፡፡ ሰብላቸው አበቃቀሉ ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ነግረውናል፡፡
አርሶ አደሩ ማሳቸውን ደጋግመው አርሰው በቂ ግብዓት ተጠቅመዋል፡፡ የአረም እና የተባይ ቁጥጥርን በየቀኑ ነው የሚያደርጉት፡፡ ውኃ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በተራ ያጠጣሉ፡፡ በተለይ በክላስተር መዝራታቸው ለአጨዳ እና ውቂያ እንደሚጠቅማቸው፣ ተባይ እና በሽታ ቢከሰት በተከታታይ ለመርጨት እና ውኃ ለማጠጣት ምቹ ነው ብለዋል፡፡ የተሻለ ምርት እንደሚያገኙም ተስፋ አላቸው፡፡
ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዓለምቀረ ይሁን የሀገራችንን ህልውና ለመጠበቅ ስንዴ አዋጪ አዝመራ ነው ብለዋል፡፡ አርሶ አደር ዓለምቀረ ሰብላቸውን የሚንከባከቡት ከግብርና ባለሙያው በሚሠጥ ምክረ ሃሳብ በመኾኑ የሰብላቸው ቁመና ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
May be an image of 2 people, grass and text
አርሶ አደሩ ዘሩ በተዘራ ከ35 እስከ 40 ቀን ድረስ ዩሪያ ጨምረዋል፡፡አረም አርመዋል፡፡ የተባይ አሰሳ እና የበሽታ ቁጥጥር ሥራቸውም የሚቋረጥ እንዳልኾነ ተናግረዋል፡፡ ሌሎች አርሶ አደሮችም የእሳቸውን ፈለግ እንዲከተሉ ይመክራሉ ፡፡ በምግብ ራስን ለመቻል ዋናው ነገር ጠንክሮ መሥራት ነው ብለዋል አርሶ አደር ዓለምቀረ፡፡
በባንጃ ወረዳ የሰንከሳ ቀበሌ የመስኖ ባለሙያ መሰረት ብሩ አርሶ አደሮች ስንዴ በክላስተር እያመረቱ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም በተደጋጋሚ የተደረጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡በቀበሌው ከ300 ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል፡፡ የግብዓት አቅርቦቱ እና አጠቃቀም ሂደቱም ተመራጭ ነው፡፡ በዚህ ዓመት 40 ኩንታል በሄክታር ለማግኘት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ በቀበሌው የተከሰተውን የቢጫ ዋግ በሽታ ለመከላከል በባሕላዊ እና በዘመናዊ መንገድ መከላከል መቻሉንም ባለሙያው አንስተዋል፡፡ አርሶ አደሮች ለሥራው የሠጡት ትኩረት ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
የባንጃ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወርቅነህ ዳኛው በወረዳው ከ2 ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ስንዴ በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ ወርቅነህ የሚገኘውን ምርት ከፍ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ በተለያዬ መንገድ ለአርሶ አደሮች ድጋፍ እየተደረገ መኾኑን አንስተዋል፡፡
በወራዳው ከ200 በላይ ዘመናዊ የውኃ መሣቢያ ሞተሮች አገልግሎት እየሠጡ ነው፡፡ በወረዳው ተፈላጊው የዘር ዓይነት ባለመቅረቡ አርሶ አደሮች የራሳቸውን ዘር እንዲጠቀሙ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡ ይህም ሰብሉን ለቢጫ ዋግ ማጋለጡን ተናግረዋል፡፡ እስካሁንም 15 ሄክታር መሬት በዘመናዊ መንገድ 45 ሄክታር መሬት ደግሞ በባሕላዊ መንገድ ከበሽታው መከላከል መቻሉን ተናግረዋል፡፡ አቶ ወርቅነህ የአረም እና የተባይ ቁጥጥር ሥራው እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞን የአትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ ውኃ አጠቃቀም ቡድን መሪ አዲስ ዓለሙ በዞኑ ከ29 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በዘር ለመሸፈን ታቅዷል ብለዋል፡፡ እስካሁን ከ27 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡ ሥራው በዩኒቨርሲቲዎች፣ በባለሃብቶች እና በወጣቶች በሥፋት እየተሠራ ነው፡፡
አቶ አዲሱ ለሥራው ትኩረት በመስጠት ለአርሶ አደሮች ሥልጠና ተሠጥቷል፣ ፕሮጀክቶችም ድጋፍ እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡
በዞኑ፦
👉448 ክላስተሮች ተደራጅተዋል፣
👉በ160 ቀበሌዎች የተደራጀ ኀይል ወደሥራ ገብቷል፣
👉2 ሺህ 337 ሞተር ፓምፕ ጥቅም እየሠጠ ነው ብለዋል፡፡
አቶ አዲሱ በ2 ሺህ 243 ሄክታር መሬት ላይ የቢጫ ዋግ በሽታ ቢከሠትም ከአንድ ማዕከል አቅራቢያ በተገዛ መድኃኒት መከላከል መቻሉን አንስተዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የመስኖ አጠቃቀም ባለሙያው ተሻለ አይናለም በክልል በምግብ ራስን መቻል እና ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚለውን መንግሥታዊ መርህ ተከትሎ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ከ720 ሺህ በላይ ሰዎች በሥራው ይሳተፋሉ ብለዋል፤ ከ 440 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ እና 298 ሺህ 151 ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ውሏል 28 ሺህ 122 የውኃ መሳቢያ ሞተሮች ጥቅም እየሠጡ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
የዘር ችግር ባለባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሩ የራሱን ዘር እንዲጠቀም ተደርጓል ብለዋል፡፡ የተባይ እና የበሽታ ቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!