በሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር እና በእገታ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡

0
154

በሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር እና በእገታ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር
ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር: ሰኔ 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር እና በእገታ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር
ሥር ማዋሉን የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።
በእገታ ወንጀል ተሳትፈዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ሰኔ 15/2013 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ገደማ የሦስት ዓመት ከሁለት ወር ሕጻን
በማገት ተሰውረዋል፡፡ በዕለቱ ከቀኑ 11፡30 ገደማ ደግሞ የሕጻኑ ወላጆች በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ
ስምንተኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ ሪፖርት አድርገዋል፡፡ ሪፖርት በሚያደርጉበት ጊዜ ከአጋቾች በኩል ለሕጻኑ ወላጆች ስልክ ተደውሎ
300 ሺህ ብር መክፈል ከቻሉ ሕጻኑ እንደሚመለስላቸው ይነግሯቸዋል፡፡
በጣቢያው የታክቲክ ወንጀል ምርመራ ክፍል ኀላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ያረጋል ተሻለ በተለይ ለአሚኮ እንዳሉት ፖሊሳዊ ጥበብን
ተጠቅሞ ሕጻን በማገት ድርጊት የተሳተፉት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥ ሥር ለማዋል ስምሪት ተደርጓል፡፡ በማኅበረሰቡ ጥቆማ
አዴትና ሰባታሚት ተብለው ወደሚጠሩ አካባቢዎች ልዩ ስምሪት በማድረግ ትናንት ከቀኑ 9፡00 ላይ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር
ሥር ማዋል ተችሏል ብለዋል፡፡
ከዋናው ተጠርጣሪ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው ሌሎች ሰባት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥ ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው
መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
ረዳት ኢንስፔክተር ያረጋል እንዳሉት ተጠርጣሪው ከማቀድና ሁኔታዎችን አቀነባብሮ ድርጊቶችን ስለመፈጸሙ እንዲሁም ሕጻኑን
አግቶ እንደተሰወረ አምኗል፡፡ ስለፈጸማቸው ድርጊቶች ሁሉ ለፖሊስ ቃል ሰጥቷል፤ ዛሬ ጠዋት 4፡00 ላይ ሕጻኑ ወደተደበቀበት
ይልማና ዴንሳ መርቶ እንደወሰዳቸውም ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሰረት 5፡15 ላይ ሕጻኑን ማግኘት ተችሏል ነው ያሉት፡፡ የለበሰው
ልብስ ከመቀየሩ ውጪ ሕጻኑ ምንም ጉዳት ሳይደርስበት መገኘቱንም ከፖሊስ ጣቢያው የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
የወንጀል ድርጊቱ በተፈጸመ በአራተኛው ቀን ሕጻኑ ለወላጆቹ እንዲመለስ ከማድረግ ባለፈ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር
ለማዋል ኅብረተሰቡ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል፤ ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የወንጀል ድርጊትን በውጤታማነት
ለመከላከል ኅብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሌላ ዜና መነሻውን ጎንደር አድርጎ በተሽከርካሪ ወደ ባሕር ዳር በሕገወጥ መንገድ ሲገባ የነበረ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ሥር
ማዋሉን የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል፡፡
በመምሪያው የኢኮኖሚ ወንጀሎች ምርመራ ክፍል ኀላፊ ኮማንደር ተዘሩ ሽባባው እንዳሉት 123 ሽጉጥ፣ 1 ሺህ 943 የብሬን
ጥይት እና 35 የቱርክ ሠራሽ ሽጉጥ ጥይት በግለሰቦች አማካኝነት በሕገወጥ መልኩ ሲዘዋወር ነው በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት
እና በፖሊስ የተቀናጀ የክትትል ሥራ ነው በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 14 በቁጥጥር ስር የዋለው፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ ሦስት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ማስረጃዎችን የማሰባሰብና ምርመራዎችን
በማከናዎን ላይ እንደሆነም ኮማንደር ተዘሩ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ለሚመለከተው የፍትሕ አካል በማቅረብ የሕግ ውሳኔ
ለማሰጠት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m