በሐሳብ ልዩነት መካከል የተጋመደ ሕዝባዊ አንድነትን መፍጠር የአማራ ሕዝብ ነባር እሴት መኾኑን ማሳየት ይገባል ተባለ፡፡

103

ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወቅታዊ ኹኔታዎች እና የቀጣይ መፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች ኮንፈረንስ በባሕር ዳር ተጀምሯል፡፡ ኮንፈረንሱ ከግንቦት 10/2015 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት ይዘልቃል ተብሏል፡፡

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ያዘጋጀው ይህ ኮንፈረንስ “ፈተናዎችን ወደ ድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን” በሚል መሪ ሃሳብ ከ1 ሺህ 400 በላይ ተሳታፊዎች ይታደሙበታል፡፡ በኮንፈረንሱ መጀመሪያ ላይ የተገኙት እና የኮንፈረንሱን ግብ እና ዓላማ ለተሳታፊዎቹ ያስተዋወቁት የአማራ ብልጽግና ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኅላፊ ዶክተር ጋሻው አወቀ ኮንፈረንሱ ውስጣዊ አንድነትን እና የፖለቲካ ከፍታን ለማምጣት ያለመ ነው ብለዋል፡፡

ኮንፈረንሱ የክልሉን ውስብስብ አሁናዊ ችግሮች በጥልቀት ገምግሞ የቀጣይ ጊዜያት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል ያሉት ዶክተር ጋሻው ጠንካራ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ እና የተስተካከለ የትግል ስልት መቀየስ ከኮንፈረንሱ የሚጠበቅ ውጤት ነው ብለዋል፡፡

ለረጂም ዘመናት የተዘሩ የተሳሳቱ ትርክቶችን ተከትሎ የሚስተዋሉ ግጭቶችን እና አውዳሚ ቀውሶችን በማረም ሥልጡን እና ዲሞክራሲያዊ የሃሳብ ትግል መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ኮንፈረንሱ የአመራሩን የሃሳብ አንድነት፣ ጽናት እና በራስ መተማመን ይጨምራል ብለዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ኃይልን የሚያሰባስብ ሠላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ የሃሳብ ትግል ማካሄድ እና የውስጠ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ትግልን ማጠናከርን ይጠይቃል ያሉት ዶክተር ጋሻው በሃሳብ ልዩነት መካከል የተጋመደ ሕዝባዊ አንድነትን መፍጠር የአማራ ሕዝብ ነባር እሴት መኾኑን ማሳየት ይገባል ነው ያሉት፡፡ ጽንፈኝነት ወቅታዊ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ችግር ነው ያሉት ዶክተር ጋሻው ጽንፈኝነትን ለመታገል በሃሳብ ልዩነት ማመን እና በጋራ መታገል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በአሁናዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጽንፈኝነት የሁሉም አካባቢዎች ችግር ነው፤ ችግሩ የአንድ አካባቢ እና ክልል ብቻ አይደለም፡፡ ጽንፈኝነትን ከአማራ ክልል ጋር ብቻ ለማያያዝ የሚሞክሩ ኀይሎችም ከስህተታቸው በፍጥነት ሊታረሙ ይገባል ነው ያሉት ዶክተር ጋሻው በመልዕክታቸው፡፡ ለውጥን ለማምጣት ትዕግስትን፣ ብስለትን እና የተረጋጋ የፖለቲካ ብቃትን ስለሚጠይቅ ኮንፈረንሱ ለአመራሩ የተሻለ መግባባትን ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!