በሃይማኖት ሰበብ ግጭት ለማስነሳት የሚጥሩ የፖለቲካ ቁማርተኞች እጃቸውን ሊሰበስቡ እንደሚገባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አሳሰበ።

0
143

በሃይማኖት ሰበብ ግጭት ለማስነሳት የሚጥሩ የፖለቲካ ቁማርተኞች እጃቸውን ሊሰበስቡ እንደሚገባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ
አሳሰበ።
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 18/2013 ዓ.ም (አብመድ) ከሰሞኑ በመትረየስ፣ በስናይፐርና በዲሽቃ በመሳሰሉ ከባድ መሳሪያዎች ጥቃት
ከተፈጸመባቸው አካባቢዎች መካከል በአንጾኪያ ገምዛ ወረዳ የሀገረማርያም ዋጨራ ቀበሌ አንዷ ናት። በዚች ቀበሌ ከመጋቢት
12/2013 ዓ.ም ጀምሮ የተፈጸመው ጥቃት ከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አስከትሏል።
የአንጾኪያ ገምዛ ወረዳ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አዋሳኝ አካባቢዎች
የተፈጸመውን ጥቃት አውግዟል። ጥቃቱ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው መሆኑን የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔው ሥራ አስፈጻሚዎች
ተናግረዋል።
የጉባዔው ሰብሳቢ ቀሲስ ሸጋው ወርቃገኝ እንዳሉት ጥቃቱ እስካሁን ታይቶ የማይታወቅ ነው። በአዋሳኝ አካባቢዎቹ የሚኖረው
ሕዝብ ተጋብቶና ተዋልዶ ያለምንም ልዩነት በሠላም፣ በመተሳሰብና በመከባበር የኖረ አሁንም እየኖረ ያለ ሕዝብ እንደሆነ
ገልጸዋል። የሰሞኑ ጥቃትም በሃይማኖትና በቋንቋ ቢለያይም በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሩ ፈጽሞ ሊለያይ የማይችልን
ሕዝብ ለመከፋፈል ታስቦ የተደረገ የፖለቲካ ቁማር መሆኑን ነው የተናገሩት።
በጥቃቱም ሰዎች ተገድለዋል፣ አካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ሕጻን አዛውንቱ ለስነልቦና ችግር ተጋልጠዋል፣ በብዙ ውጣውረድ
የተገኘ ሀብትና ንብረት ለዘራፊ ሲሳይ እና ለእሳት ራት መሆኑንም ነው ቀሲስ ሸጋው የገለጹት።
የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔው ምክትል ሰብሳቢ ሸህ አልይ ሙስጠፋ እንዳሉት ደግሞ ከ1983 ዓ.ም ወዲህ በተፈጠረው
የከፋፋይ የፖለቲካ ሥርዓት በሕዝብ ላይ አሰቃቂ ግፍና በደል እየደረሰ ነው። ከሰሞኑ በገጠመው ችግርም ጥቃት አድራሹ ቡድን
የተደራጀ በመሆኑ ሰዎች ሊቋቋሙት አልቻሉም ነው ያሉት። ጥቃቱን የብሔርና የሃይማኖት መልክ ለማስያዝ የሚደረግ
የፖለቲከኞች ሴራ መሬት ላይ ያለውን ሀቅ እንደማይወክልም ተናግረዋል። ለዚህም ከሰሞኑ በተፈጠረው ጥቃት አማራዎችን
ከሞት የታደጉ ኦሮሞዎች መኖራቸውን ለማሳያነት አንስተዋል።
የጉባዔው ጸሐፊ ውብሸት ማሞ ጥቃቱ ለአካባቢው ሰዎች የማይመጥን፣ እንደሚወራው ከሕዝብ የመጣ ሳይሆን የተጠና የሴራ
ፖለቲከኞች ውጥን መሆኑን ገልጸዋል። የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝብን በብሔርና በሃይማኖት ከፋፍሎ ሀገርን ለመበተን የታቀደ
እኩይ ተግባር እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።
ሥራ አስፈጻሚዎቹ እንዳሉት የመንግሥት ዋነኛ ተግባር የዜጎችን ሰላምና የመኖር ዋስትና ማረጋገጥ ቢሆንም ጥቃቱን ቀድሞ
ማስቀረት አልቻለም። ጥቃቱ ከተጀመረ በኋላም ፈጥኖ የማረጋጋት ርምጃ ባለመውሰዱ ከፍተኛ ቀውስ ደርሷል። የመንግሥት
ቸልተኝነት ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን ያነሳው የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔው ሊታሰብበት እንደሚገባም አሳስቧል። መንግሥት
በየአካባቢው የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮችን ፈጥኖ በመቀልበስና በማረጋጋት ለዜጎች ከለላ እንዲሆንም ጠይቀዋል።
የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችም የተፈጠረውን ችግር በማረጋጋትና ማኅበረሰቡ አካባቢውን እንዲጠብቅ የማስተማር
ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መክረዋል። ማኅበረሰቡም የቆሰሉ ወገኖች እንዲያገግሙ፣ ሀብትና ንብረታቸው የወደመባቸውም
እንዲቋቋሙ መተጋገዝ አለበት ብለዋል።
ሥራ አስፈጻሚዎቹ ፖለቲካን ከሃይማኖት መለየት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11 መደበኛ ጉባዔ ላይ አንዳንድ የሕዝብ እንደራሴዎች ተጨማሪ እልቂት
እንዲፈጠር ያደረጉትን ቅስቀሳም ሥራ አስፈጻሚዎቹ አውግዘዋል።
እንደራሴዎቹ ኃላፊነታቸውን በመዘንጋት ወደ ትርምስ የሚያስገባ ንግግር ማድረጋቸው አሳሳቢና አሳዛኝ እንደሆነ ተናግረዋል።
ጽንፈኛ ፖለቲከኞች ሕዝብ የሰጣቸውን ስልጣን ያለ አግባብ ተጠቅመው ኢትዮጵያውያንን በብሔርና በሃይማኖት ለመከፋፈል
የመረጡት ፖለቲካዊ ስልት እጅግ አደገኛ፣ ያልተለመደና ከኢትዮጵያዊነት እሴት ያፈነገጠ እንደሆነም አመላክተዋል።
መንግሥት የሀገርን ሕልውና የሚፈታተን አመለካከት ያላቸውን ግለሰቦች በአንክሮ ሊመለከታቸው ይገባል፤ ሕዝብን በሃይማኖት
ወደ ግጭት ለማስገባት የሚጥሩ የፖለቲካ ቁማርተኞችም ከሃይማኖት ላይ እጃቸውን እንዲያነሱ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል መንግሥትም ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን በሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አዋሳኝ
አካባቢዎች ያለውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ የአንጾኪያ ገምዛ ወረዳ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሥራ አስፈጻሚዎች
ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ – ከመኮይ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here