በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ አማራዎች በአማራ ሕዝብ ጥቅም ጉዳይ በአንድነት መሥራት እንደሚገባ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ጠየቁ፡፡

0
64

ኢኮኖሚው የዳበረ ሕዝብ ለመፍጠር የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡

በክልሉ ኢንቨስትመንት፣ ልማት እና የአማራ አቀፍ ልማት ማኅበር (አልማ) ድጋፍ አንዲሁም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት በአትላንታ- ጆርጅያ አሁን ተጀምሯል፡፡

በአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ፈንታ በተመራው ውይይት በአትላንታ እና አካባቢው የሚኖሩ አማራ ባለሀብቶች፣ ምሁራን፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው፡፡

የክልሉን የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ የአልማ የሦስት ዓመታት የለውጥ ዕቅድ፣ የአማራ መደራጀት እና መደጋገፍ ፋይዳዎች እንዲሁም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ ቀርቧል፡፡

አቶ ዮሐንስ ቧያለው ለተሳታፊዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት የተለያዬ አመለካከት ቢኖርም በአማራ ሕዝብ ጥቅም ጉዳይ በአንድነት መሥራት እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ ለዚህም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ወገኖች የጋራ በሚያደርጉ የሕዝቡ ጉዳዮች መተባበር መሠረታዊ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ አማራዎች እራሳቸውን ጠቅመው የሕዝቡን ኑሮ የመቀዬር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ነው አቶ ዮሐንስ የጠየቁት፡፡ ይህን ዕውን ለማድረግ ደግሞ ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠር እና ቀጣይነት ማድረግ የሚያስችሉ አሠራሮች እንደሚኖሩ አስገንዝበዋል፡፡

የአልማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ፈንታ ደግሞ ጠንካራ ተቋማዊ አሠራሮችን በመፍጠር ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኙ ተግባራትን ለሕዝቡ ለመሥራት መደጋገፉ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም እንደ አልማ፣ የአማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር፣ አማራ ኢንሹራንስ ባሉት እና በሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሳተፉ ለተወያዮቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በየሙያ መስኮች ለሕዝቡ እገዛ ማድረግም ለመደጋገፍ ሌላው አማራጭ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

አልማ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ለመሥራት ስላቀዳቸው ተግባራት ባቀረቡት ማብራሪያም በአዲስ አበባ የአማራ የባህል ማዕከል ግንባት፣ በክልሉ ዘጠኝ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች እና በመቶዎች የሚቆጠሩ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሥራ እንዲሁም ሌሎም ማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት እንደተካተቱ አስረድተዋል፡፡ ለስኬታማነቱ በጋራ እንዲሰሩ እና ይህንን ማድረግ እንደሚቻልም አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡

ውይይቱ “የአማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል መሪ መልዕክት ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡

ዘጋቢ፦ አስማማው በቀለ – ከአትላንታ- ጆርጅያ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here