በሀገራዊ ምክክሩ ከ40 በላይ ፓርቲዎች አብረውን ለመሥራት ተስማምተዋል።

0
100

ባሕርዳር፡ ጥር 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከ40 በላይ የሚኾኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኮሚሽኑ ጋር ለመሥራት መስማማታቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እንደተናገሩት፤ ተፎካካሪዎቹን እና ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ በምርጫ ቦርድ ከተመዘገቡት 53 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ከ40 በላይ የሚኾኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኮሚሽኑ ጋር ለመሥራት ተስማምተዋል።

ከ40 በላይ ከኾኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብረን ለመሥራት ስምምነት ላይ እስክንደርስ ድረስ የራሳቸው ጥርጣሬ ነበራቸው ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ አንዳንዶቹ በአዋጁ አቀራረጽ ሂደት ላይ እንዲሁም በኮሚሽኑ ስም ላይ ጥያቄዎች እንደነበሯቸውም ነው የተናገሩት። በሂደት በተሠሩ ሥራዎች ከ53ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ከ40 በላይ የሚኾኑት አብረዋቸው ለመሥራት የተስማሙ ሲሆን፤ በቅርብ ጊዜ ውስጥም የስምምነት ማዕቀፍ የሚፈራረሙ መኾኑን ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ አብሮ ለመሥራት ፍላጎት ካላሳዩት ከአስር የሚልቁ ፓርቲዎች ጋርም አብሮ ለመሥራት ጥረቶች መቀጠላቸውንም ተናግረዋል።

“አብረውን ለመሥራት ፈቃደኛ ካልሆኑት ፓርቲዎች ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እየተገናኘን እኛ ማን እንደኾንን እንዲሁም ሥራችን የት ድረስ እንደሚሄድና የሥራ ኃላፊነታችን ምን ምን እንደሆነ በማስረዳት ላይ እንገኛለን ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ እኛ የውይይትን ሥራ ማመቻቸትና ማሳለጥ እንጂ ወሳኞች ስላልሆንን ይህንን እያሳወቅናቸው ነው” ብለዋል።

አብላጫው ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ብናገኝም አብረው ለመሥራት ፍላጎት ያላሳዩትም ኢትዮጵያ ሀገራቸው ነችና ያልሰሙንና ያልፈለጉን ጥቂት የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው ብለን እነሱን ወደ ኋላ መተው የለብንም።

ያልተቀበሉን ወይም የተቃወሙን የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደፊት ሁኔታዎች ከተመቻቹ ሀገር የሚመሩና የሚያስተዳድሩ ስለሆኑ ሕዝብ የተዋደደበትንና የተፋቀረበትን ጠንካራ ሀገርን መምራት ለፖለቲካ ፓርቲዎችም ትልቅ ዕድልና ጸጋ ይመስለኛልም ነው ያሉት።

ፕሮፌሰሩ ከፖለቲካ ፓርቲዎችም ባሻገር የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፤ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የአካል ጉዳተኛ ማኅበራት፣ የሴቶች ማኅበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም እዚህ ሀገር ያሉትን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተወካይ አምባሳደሮችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን የሚመሩ ኃላፊዎችን ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን ከተቋቋመ ዘጠኝ ወራትን ያስቆጠረው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቅቡልነቱ እየሰፋ መኾኑንና ወደፊትም ከዚህ በላይ ተቀባይነት እንደሚኖረው ያላቸውን ተስፋም ተናግረዋል። ዘገባው የኢፕድ ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!