ቅርሶችን በመጠበቅ እና በማልማት የማኅበረሰብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለጸ።

67
ባሕር ዳር :መጋቢት 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ቅርሶችን በመጠበቅ፣ በመንከባከብ እና በማልማት የማኅበረሰብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክቶሬት ተወካይ ዳይሬክተር ኢንጅነር ጌታቸው ተካልኝ ተናግረዋል። ኢንጅነር ጌታቸው ይህንን ያሉት ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ከአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር በባሕርዳር ከተማ ባዘጋጀው የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ ላይ ነው።
ኢንጅነር ጌታቸው የስልጠናው ዓላማ በክልሉ የተለያዩ ዞኖች የሚገኙ የቅርስ ባለሙያዎች በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የቅርስ እንክብካቤ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል ነው ብለዋል። ዕድሜ ጠገብ የኾኑ ቅርሶችም ተገቢውን ጥገና በተገቢው ባለሙያ እንዲያገኙ ለማድረግ መኾኑን ተናግረዋል።
ኢንጅነር ጌታቸው በርካታ ቅርሶች ጉዳት ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል። እነዚህ ቅርሶች ለትውልድ እንዲሻገሩ ለማድረግ ተገቢውን ጥበቃ እና እንክብካቤ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ቅርሶችን በመጠበቅ እና በማልማት የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ እየተሠራ ሥለመኾኑም አመላክተዋል።
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አቶ አባይነው መንግስቱ በአማራ ክልል የሚገኙ በርካታ ዕድሜ ጠገብ ቅርሶች ከእርጅና ጋር በተያያዘ የመፍረስ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ገልጸዋል። ስልጠናው ያስፈለገበት ምክንያት በቅርሶች ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ እና ከቅርሶች በሚገኝ እሴት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ነው ብለዋል።
አቶ አባይነው በአማራ ክልል የሚገኙ ቅርሶችን አልምቶ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተሠራው ሥራ በቂ እንዳልኾነ ገልጸዋል። ስለዚህ በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ የተሰማሩም ኾነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲሳተፉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አቶ አይቸው አዲሱ በከተማው የሚገኙ ቅርሶች ዕድሜ ጠገብ ከመኾናቸው የተነሳ በጉዳት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። አቶ አይቸው እየተሰጠ የሚገኘው የቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ ስልጠና ወደተግባር ተገብቶ ሲሠራበት የቅርሶችን ህልውና የሚታደግ እንደሚኾንም ተናግረዋል። ሁሉም የቅርስ ባለሙያዎች ያለመሰልቸት ክትትል ማድረግ እና ሕዝቡንም በማንቃት የቅርሶችን ደህንነት መጠበቅ አለበትም ብለዋል።
በሰሜን ወሎ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ምዝገባ እና ቁጥጥር ባለሙያው አቶ ሙላቱ አራጋው ከስልጠናው ያገኙትን የቅርስ እንክብካቤ ዕውቀት በተግባር በመተርጎም ለቅርሶች ጥገና የበኩላቸውን ሙያዊ አበርክቶ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል። ቅርሶችን ለመጠገን በሙያው የተካነ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልግ የጠቀሱት አቶ ሙላቱ ማኅበረሰቡ ለቅርሶች ካለው ቀናኢነት የተነሳ በዘልማድ ከመጠገን መታቀብ እንዳለበትም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!