“ቅሬታችን በወቅቱ ከነበረው ትህነግ መራሹ ሥርዓት ጋር እንጂ ከሀገራችን ጋር ስላልነበር ዛሬም ለዳግም ግዳጅ ተዘጋጅተናል” መቶ አለቃ ማርየ ዘገየ

0
230

ጥቅምት 04/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ባንዳ እና የባንዳ ሥርዓት የበላይነት በሚወስዱበት ሀገር ውስጥ የሀገር ባለውለታዎች ከሹመት ይልቅ መሳደድ፤ ከጥቅም ይልቅ መጎዳት ይደርስባቸዋል፡፡ የባንዳዎች ጀግናን የማሳደድ እና የማምከን ሴራ ሀገርን ሲያቆረቁዝ እንደነበር በኢትዮጵያ የነጻነት ተጋድሎ ታሪክ ውስጥ ውስጠ አዋቂ የነበሩ ሁሉ የሚገነዘቡት ሀቅ ነው፡፡ ጀግና በነፍሱ ተወራርዶ በሚገነባት ኢትዮጵያ ውስጥ ፈሪ በምላሱ የሚቦረቡራት ኢትዮጵያ “የእናት ሆድ ዥንጉርጉር” እየተባለም ሲተረት ኖሯል፡፡

በኢትዮጵያ የመከራ ጊዜያት ከራሳቸው በላይ ለሚወዷት ሀገር ነፍሳቸውን ሳይቀር አሳልፈው የሰጡ የቁርጥ ቀን ልጆች እንደ ቧልት ተረስተው የድል አጥቢያ ጀግኖች በምላሳቸው የሚቆሏት ኢትዮጵያ ተረት ሳትሆን እውነት እንደነበረችም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተደጋግሞ ታይቷል፡፡ የተለየ ነገር ቢኖር በሽብርተኛው ትህነግ ዘመነ ሥልጣን የባንዳ ሥርዓት አራማጆች መንግሥታዊ መዋቅር ኖሯቸው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ኑባሬ መሆናቸው ብቻ ነው፡፡ “ሳይደግስ አይጣላም” እንደሚባለው መልካሙ ነገር ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ስለሀገራቸው የደረሰባቸውን ግፍ፣ መከራ እና መገፋት እንደ ምርቃት አሜን ብለው ተቀብለው ሀገራቸው ዳግም ስትፈልጋቸው ርቀው አለመራቃቸው ብቻ ነው፡፡

በየዘመናቱ እንደነበሩት ባንዳዎች እኩይ ሴራ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ “ጀግና ከማህጸንሽ ይንጠፍ” ተብላ ተረግማ ከመከራዎቿ በአንዱ ወድቃ የምትቀርበት ታሪኳ ይጎላ ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ አይሆን ዘንድ “ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን ሊቀይር አይቻለውም” ተብሏልና ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ከነጻነት ከፍታ እንዳይወርዱ ሥሪታቸው ታድጓቸዋል፡፡

መቶ አለቃ ማርየ ዘገየ የእናት ኢትዮጵያ የቀድሞ ሠራዊት አባል ናቸው፡፡ ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ በዘለቀው ምድራዊ ቆይታቸው ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የሚሆነው እድሜያቸው በተለያዩ ወታደራዊ ሙያዎች ያለፈ ነው፡፡ ከተራ ወታደርነት እስከ መካከለኛ አመራርነት በቆዩበት የወታደር ቤት አገልግሎታቸው ሀገራቸው እና ሕዝባቸው የጣሉባቸውን ኅላፊነት በቅንነት ተወጥተዋል፡፡

በውትድርና ቆይታቸው በተዋጊነት እና በአዋጊነት የተሳተፉት መቶ አለቃ ማርየ ከሚወዱት የውትድርና ሙያቸው የሚለያቸው ክስተት መጣ፡፡ ወቅቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሽብርተኛው ትህነግ አባላት የእርስ በእርስ ክህደት ሊፈርስ ቋፍ ላይ የቆመበት ነበር፡፡ 1993 ዓ.ም ላይ በከፍተኛ መኮንንኖች ሰብሰባ ላይ ሴረኛው እና ሽብርተኛው ትህነግ እጁን በእጁ ቆረጠ እና ወታደሩ በተጠንቀቅ ላይ እንዲቆም ትዕዛዝ ተላለፈ፡፡ “በከፍተኛ መኮንንኖቹ ስብሰባ ላይ ከከሃዲው እና ሽብርተኛው ትህነግ መስራቾች አንዱ እና በወቅቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበረው ክንፈ ገብረመድህን በሽጉጥ መመታት በሠራዊቱ ውስጥ ውዝግብ ፈጠረ” ይሉናል ባለታሪካችን መቶ አለቃ ማርየ ዘገየ፡፡ ይህም ክስተት ተከትሎም መቶ አለቃ ማርየን ጨምሮ የሠራዊቱ መካከለኛ አመራሮች እና የክፍል ኅላፊዎች ለ15 ቀናት የዘለቀ ጥልቅ ውይይት በሽሬ አካሄዱ፡፡ ይህ ለሁለት ሳምንታት የዘለቀ ወታደራዊ ጥልቅ ውይይት ከራሳቸው ውጭ ያሉ የሠራዊቱ አባላት በሽብርተኞቹ የትህነግ ወታደሮች እና አመራሮች ላይ “ሰምበር አልባ ምት” ያሳረፉበት ነበር ብለዋል መቶ አለቃ ማርየ፡፡

እስስቷ ትህነግ ከግምገማ ማግስት የለውጥ አራማጅ ወታደሮችን ከሙያቸው የምታርቀበትን ሴራ መሸረቧን ቀጥላ ነበር፡፡ በመቀጠልም “ተቀናሽ የሠራዊት አባላት” የሚል ስትራቴጂ ነድፋ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከጉድ አውጡኝ ያለቻቸውን የሠራዊቱን አባላት ሰበብ እየፈጠረች ዐይናችሁን ለአፈር ማለት ቀጠለች፡፡ “ከሁለት ሳምንቱ ግምገማ በኋላ እርስ በእርሱ ከሚበላላ እና ከማይተማመን ቡድን ጋር መቀጠል የለብንም የሚል ውሳኔ ላይ ደርሰናል” የሚሉት መቶ አለቃ ማርየ ይህ ግን ለሴረኛው እና ሽብርተኛው ትህነግ ቡድን አባላት እና አመራሮች ሰርግና ምላሽ ነበር የሆነላቸው ይላሉ፡፡

በመቀጠለም መልቀቂያ የጠየቀውን ሁሉ ያለ ጡረታ ከ6 ሺህ እስከ 4 ሺህ ብር እየወረወሩ ከምንወደው ሙያችን ነጠሉን ብለዋል፡፡ ይህ ሂደት ግን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአማራ ሕዝብ ዘንድ የውትድርና ሙያ በጎሪጥ እንዲታይ መነሻ እንደሆነ እነመቶ አለቃ ማርየ ያምናሉ፡፡ ከውትድርና ሙያ በተጠና ታክቲክ የተነጠሉት እነመቶ አለቃ ማርየ የሽብርተኛው ትህነግ ረጂም እጅ በተቀላቀሉት ማኅበረሰብ ዘንድ እንኳን የክብር ቦታ እንዳያገኙ አድርጓቸው ቆይቷል፡፡ “በተመለስኩበት ወረዳ የጥበቃ ሥራ እንኳን እንዳላገኝ ልዩ ልዩ መሰናክሎች ይደረደሩ ነበር” የሚሉት መቶ አለቃ ማርየ ቅሬታየ ሁሉ በሥርዓቱ እንጂ በሀገሬ እና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ግን ሆኖ አያውቅም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

መቶ አለቃ ማርየ እንደሚሉት ሽብርተኛው ትህነግ በደረሱበት ሁሉ መሰናክል ሲያበዛ በኢትዮጵያ እና በአማራ ሕዝብ ላይ ቂም የሚቋጥሩ መስሎት ነበር፡፡ ነገር ግን “ቅሬታችን በወቅቱ ከነበረው ትህነግ መራሹ ሥርዓት ጋር እንጅ ከሀገራችን ጋር ስላልነበር ዛሬም ለዳግም ግዳጅ ተዘጋጅተናል” ነው ያሉት፡፡ አሸባሪው የትህነግ ርዝራዦች አማራን ያክል ሕዝብ ጠላት ብለው ፈርጀው ቤተ መንግሥት እንደማይዘልቁ ያውቁታል ያሉት መቶ አለቃ ማርየ አማራን ካላዳከሙ ድጋሜ ስልጣን ላይ እንደማይቆናጠጡ ስለሚያስቡ ትግላቸው ከአማራ ሒሳብ ማወራረድ ሳይሆን አማራን ማውረድ ነው ብለዋል፡፡

የአማራን እና የኢትዮጵያን ሕልውና በወታደራዊ ሙያቸው ለመታደግ እና ትግሉን ለማገዝ ሽብርተኛው ትህነግ ትናንት የፈጠረብኝን ቁስል ማከክ ግድ አይለኝም ነው ያሉት፡፡ የ60 ዓመቱ የጦር መቶ አለቃ ላለፉት ዓመታት ሕይዎትን ከሚወዱት ወታደራዊ ሙያ ተነጥለው በሌላ መንገድ ቢያጣጥሙም የሀገራቸውን ጥሪ ሰምተው እና አምስት ልጆቻቸውን ስለሀገራቸው ትተው ግንባር ድረስ ዘምተዋል፡፡ ነገ ሀገራቸው ወደ ቀደመ ሰላሟ ስትመለስ ደግሞ ዛሬ ስለሀገር ሲሉ ወደ ተዋቸው ቤተሰቦቻቸው ይመለሳሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ግን ሽብርተኛው ትህነግ ከኢትዮጵያ በተለይም ከአማራ ሕዝብ ትከሻ ላይ ላይመለስ ሲወርድ እንደሆነ ለራሳቸው ምለዋል፡፡ ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከገረገራ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m