ቃና ዘገሊላ!

0
103

ቃና ዘገሊላ

 

ባሕር ዳር:ጥር 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በቃና ዘገሊላ የጎደለው ሞልቷል፣ የጠፋው ተገኝቷል፣ የተሰወረው ተገልጧል፡፡ በገሊላ አውራጃ የመጀመሪያው ተዓምር፤ ቃናው የሚጥም ወይን በዶኪማስ ቤት ተገለጠ፡፡ “ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል ከሰከሩም በኋላ መናኛውን ። አንተ ግን መልካሙን እስከ አኹን አቆይተኸል” እንዳለ አሳዳሪው ባለቤቱን ጠርቶ፡፡ የወይን ጠጁ ባለቤት ግን የሕይዎት ኹሉ ባለቤት የኾነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነበር ይላሉ አበው ሲያስተምሩ፡፡

ከዮርዳኖስ ወደ ቆሮንቶስ ወርዶ ጥምቀቱን በጸሎት ያጸናው ክርስቶስ ኢየሱስ እስከ ቀራኒዮ የሚዘልቀውን እውነተኛ የሕይዎት አስተምህሮ በሰርግ ቤት ውስጥ ታድሞ በተዓምራት ጀመረ፡፡ ከእናቱ እና ደቀ መዛሙርቱ ጋር ሳለ ፤ የወይን ጠጅ ያለቀበትን ሰርግ አይታ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም “ወይን ጠጅ እኮ አልቆባቸዋል” ስትል ውኃውን ወደ ወይን ቀይሮ የእናቱን ልመና በትሕትና ፈጸመ ያሉን በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የደብረ ቅዱሳን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ የኾኑት መላከ ምሕረት ግሩም አለነ ናቸው፡፡

መምህር ግሩም እንደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ቃና ዘገሊላ ሁለት ትርጉም አለው ይላሉ፡፡ የመጀመሪያው በገሊላ አውራጃ የምትገኝ እና ቃና የምትባል መንደር ናት፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ የገለጸው የመጀመሪያው ተዓምር መጠሪያ ስያሜ ተደርጎም ይወሰዳል ብለውናል፡፡ ቃና ዘገሊላ ኢየሱስ ክርስቶስ በዶኪማስ ቤት ተገኝቶ ውኃን ወደ ወይን ጠጅ የቀየረበትን ተዓምር የገለጠበት እና ጋብቻን የባረከበት ዕለት ነው ይላሉ፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወርዶ በደቀ መዝሙሩ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፡፡ ከጥምቀቱ በኋላም ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ወርዶ 40 ቀን እና 40 ሌሊት በጾም እና በጸሎት ተወስኖ ቆየ፡፡ ከገዳመ ቆሮንቶስ ወጥቶ የገሊላ ክፍለ ሀገር የምትሆን ቃና ወደተባለች ቦታ አቅንቶ ከእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም እና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሰርግ ላይ ታደመ ይላሉ፡፡

ቃና ዘገሊላ የካቲት 23 ቀን የተፈጸመ ተዓምር ነው ያሉን መላከ ምሕረት ግሩም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በዓሉን ከጥምቀት በዓል በኋላ ጥር 12 ቀን ታከብረዋለች ብለውናል፡፡ ምክንያቷ ደግሞ የቃና ዘገሊላ በዓል ውኃ ወደ ወይን ጠጅ የተቀየረበት የውኃ በዓል በመሆኑ ከጥምቀት በዓል ጋር አስተሳስራ ለማክበር ነው ይላሉ፡፡ የውኃ በዓል ከውኃ በዓል ጋር ይከበራል በሚል፡፡

የቃና ዘገሊላ በዓል ካለማወቅ ወደ ማወቅ መሸጋገር ነው የሚሉት መምህሩ ባዶ የነበሩ ጋኖች በውኃ ተሞሉ፤ ውኃው ደግሞ ወደ ወይን ጠጅ ተቀየረ፡፡ የሰው ልጅም ወደ ፈጣሪው ሲቀርብ ንጹህ ሆኖ እና እንደ ሕጻን አላዋቂ ኾኖ ነው፡፡ የሰው ልጅ ሕይዎት ሙሉ የሚሆነው ውኃ እንደተሞሉት ጋኖች በእግዚዓብሔር ተዓምራት እና ትምህርት ነው፡፡ በመንፈሳዊ ሕይዎታችን ስንበረታ እና ስንጠነክር ደግሞ በትምህርቱ እና በምህረቱ ሙሉ የኾነው ሕይዎታችን በሰማይ እንደ ወይን ጠጅ የጠነከረ እና ጣፋጭ ይኾናል ነው ያሉት መምህር ግሩም፡፡

መላከ ምሕረት ግሩም ሌላው ከቃና ዘገሊላ የምንማረው የሰው ልጅ የሌሎቹን ጭንቀት እና ጉድለት አይቶ ማዘንን ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም፤ ልመናን በቸርነት፤ መሻትን በቅንነት መፈጸምን ደግሞ ከክርስቶስ ኢየሱስ ክርስቲያኖች ኹሉ ይማሩበት ዘንድ ግድ ይላል ይላሉ፡፡ ዛሬ ዓለማችን ብዙ የጎደሏት ነገሮች አሉ፤ ዛሬ ሕይዎታችን የሌሎችን ድጋፍ እና ብርታት ይሻል እናም አንዱ የሌላውን ጎደሎ፤ ወንድም የወንድሙን ክፍተት መሙላት ክርስቲያናዊ ተግባር እና ግዴታ ነው ብለዋል፡፡

የቃና ዘገሊላ አስተምህሮ እና ትውፊትም የክርስቶስን ተዓምራት ማየት እና ወደ እግዚዓብሔር መጠጋት ነው ይላሉ፡፡ ክርስቲያኖች ክርስትናን መርሐቸው ሲያደርጉ ነገሮች ኹሉ በፈተና እና በመከራ ይሞላሉ የሚሉት መላከ ምሕረት የክርስትና መለያው ከፈተና በኋላ አሸናፊነት፤ ከመከራ ማግስት ልጅነት መኖሩን በማመን በፈተና ወቅት ጽናትን በመከራ ጊዜ ትዕግስትን መላበስ ነው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!