ቃና ዘገሊላ

0
116

ባሕር ዳር፡ ጥር 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ቃና ዘገሊላ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ የመጀመሪያውን ታምሩን የገለጸበት ቦታ ነው፡፡ ቃና ዘገሊላ ሁለት ትርጉም አለው፡፡ አንደኛው በገሊላ አውራጃ የምትገኝ ቃና የተባለች መንደር ስትኾን ሁለተኛው ኢየሱስ ክርስቶስ የገለጸው የመጀመሪያ ተዓምር ስያሜ ነው፡፡ ቃና ዘገሊላ ኢየሱስ ክርስቶስ በዶኪማስ ቤት ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን የቀየረበትና ጋብቻን የባረከበት ዕለት ነው፡፡ ቃና ዘገሊላ በዕለቱ የተደረገውን ተዓምር ይዞ የበዓል ስያሜ ኾኖ መሰጠቱን መምህር ገብረመድህን እንየው ነግረውናል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በደቀ መዝሙሩ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፡፡ ሳይውል ሳያድር በገዳመ ቆሮንጦስ ገብቶ 40 ቀንና 40 ሌሊት ፀለየ፡፡ ከገዳመ ቆሮንቶስ ሲወርድ የካቲት 23 ቀን በዶኪማስ ቤት ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን የቀየረበት የመጀመሪያው ተዓምር ነው ብለዋል መምህር ገብረመድህን፡፡

እንደ መምህር ገብረመድህን ገለጻ በዶኪማስ ቤት ድንግል ማርያም፣ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ ተገኝተው ነበር፡፡ ይህ ተዓምር የካቲት 23 ቀን ይፈጸም እንጅ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በዓሉን ጥር 12 ቀን ከጥምቀት በዓል ጋር አስተሳስራ በደመቀ ሁኔታ ታከብራለች፡፡ የቃና ዘገሊላ በዓልም የውኃ በዓል ስለሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም ከጥምቀት በዓል ጋር አስተሳስራ የምታከብርበት ምክንያቱ ይህ መሆኑን መምህሩ ነግረውናል፡፡

መምህር ገብረመድህን እንዳሉት ምዕመኑ ከቃና ዘገሊላ ትምህርት መውሰድ ይገባዋል፡፡ የመጀመሪያው ምሳሌነቱ ካለማወቅ ወደ ማወቅ መምጣትን ነው፤ ጋኖቹ ባዶ ነበሩ በወይን ተሞልተዋል፡፡ እኛም የሰው ልጆች በጥበብ ልንሞላ ይገባል፡፡ ሌላው አክብሮትንና አንድነትን እንማርበታለን፤ ዶኪማስ ድንግል ማርያምን በሰርጉ እንድትታደም ሲጠራት ብቻዋን አልነበረም ከልጇ ጋር እንጅ፤ ልጇን ጠርቶ ዝም አላለም ደቀ መዛሙርቱን ጨምሮ ጠርቷል፡፡ እናም ይህን በዓል ስናከብር አንዳችን ለአንዳችን ያለንን ክብር ልናሳይበት ይገባል ብለዋል፡፡

መምህር ገብረመድህን ከቃና ዘገሊላ ልንማር ይገባል ያሉት ሌላው ጉዳይ አንዳችን የአንዳችንን ጭንቀት መገንዘብ፣ መረዳት፣ ተረድተን ዝም ማለት ሳይሆን መፍትሔ ማፈላለግና ማገዝ እንደሚጠበቅብን ነው፡፡ ምክንያቱም ድንግል ማርያም ሰርጉን ሲያስተናግዱ የነበሩ ሰዎች ሲጨነቁ ዓይታ ለልጇ “ወይኑ አልቆባቸዋል” አለችው፤ እርሱም መፍትሔ ሆናቸው፡፡

ምዕመኑ በዓሉን ለማክበር ሲወጣ በልማድ ሳይሆን አስተምህሮውን በማወቅ፣ ያወቅነውን ሳንበርዝ በመቀበል፣ የተቀበልነውን ለሌሎች በማስተላለፍ፣ ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን በመጠበቅም መሆን እንዳለበት መምህሩ አስረድተዋል፡፡

መምህር ገብረመድህን ቃና ዘገሊላን ስናከብር የጋብቻን ክቡርነት መረዳት ይገባልም ብለዋል፡፡

እንኳን አደረሳችሁ፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ፎቶ፡- ከድረ ገጽ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/