ቀድሞ በነብያት የተነገረው ሁሉ ይፈፀም ዘንድ ግድ ነበር!

0
247

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሆሳዕና እልልታ በቀራኒዮ ዋይታ ይደመደማል፡፡ ከዋክብት ይረግፋሉ፣ ጸሃይ ብርሃኗን ስትከለክል፣ ጨረቃ ደም ትለብሳለች፡፡ ሐዘን ከሰማይ እስከ ጸርሃ አርያም ሁሉ ይሆናል፡፡ ምድር የበረታ መናዎጽ ያጋጥማታል፤ መካነ መቃብራት ይከፈታሉ፡፡ ከሰማይ የሚወርደው ድምጽ በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ይረብሻል፡፡
አይሁዳዊያን ሳይቀር ባዩት ነገር ተደናግጠው እና በሰሩት ሰህትት ተጸጽተው “በእርግጥም ይኽ ሰው ጻዲቅ ነበር” ለማለት ይገደዳሉ፡፡ ይኽ ሁሉ አርብ ወደ ማታ የሚሆን የመዳን ቀን ተብሲር ነው፡፡ ለበረታ ከፍጻሜው በኋላ አዳም ሲመረመር ዲያቢሎስ ሲታሰር ያያል፡፡
አርብ የብሉይ ኪዳን ፍጻሜ እና የአዲስ ኪዳን ጅማሬ ናትና የማይታመመው ይታመማል፣ የማይሰቃየው ይሰቃያል፣ የማይሞተው ሞቶ ሞትን ድል ያደርጋል፡፡ ያለደሙ ድኅነት የሌለው አዳም ብቸኛ ተስፋው ይህንን የመዳን ቀን መጠባበቅ ነበር፡፡ የሰው ልጅ የሲኦል ባርነት እና ግዞት በክርስቶስ ደም ታትሞ የእዳ ደብዳቤው ይቀደዳል፡፡
የጸሃፍት ፈሪሳዊያን ግብዝነት የወለደው ግርፋት፣ ስድብ እና እንግልት በደሙ ፍጻሜውን ሲያገኝ በከንቱነታቸው ይሸማቀቃሉ፡፡ መጻጻ ግተው፤ የሾክ አክሊል ደፍተው የልባቸው ያልደረሰው አሳዳጆች በትዕቢት ጎኑን በጦር ወግተው በደሙ የዐይን ብርሃናቸውን ያገኛሉ፡፡ ግብዝነት እና ጥላቻ ከዐይነ ስውርነት በላይ ይጋርዳሉና በተዓምራቱ እየተደረገላቸው እንኳን ከስህተታቸው አይታቀቡም፡፡
በነብያት ቀድሞ የተነገረው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ግድ ነበርና የሚሆነው ሁሉ ከመሆን የሚያግደው ኃይል አልነበረም፡፡
ክቡር ነፍሱ በክብር የተለየችው ክቡር ስጋው ከመስቀል ላይ ሳይወርድ የአሸናፊነቱን ምልክት ለዓለሙ ሁሉ ያሳያል፡፡ ልደቱን በከዋክብት ብርሃን ተመርታ የተቀበለችው ዓለም ሞቱን እስከ ትንሣኤው በጨለማ ውስጥ ሆና መርዶዋን ትሰማለች፡፡
የክርስቶስ ትህትናው እስከ ፍጻሜው ዘልቆ “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ሲል ጥላቻን በፍቅር፤ በደልን በይቅርታ ድል ይነሳዋል፡፡ የቤተልሄሙ ሕፃን የቀራኒዮ በግ ሆኖ ይቀርባል፡፡ የግብጽ ምድሩ ስደተኛ የሲኦል ወታደር ኾኖ የ5 ሺህ 500 ዓመታት የሲኦል ውስጥ ግዞተኞችን ነፃ ያወጣል፡፡ የቆረንጦሱ ባህታዊ የምኩራቡ ረቢ ሆኖ በቃሉ ፈውስን በእጆቹ ታምራትን ይፈጽማል፤ ያስተማረውን ሁሉ ደግሞ በተግባር ሳይሸራርፍ እና ሳይሽር ፈጽሞት ያዩታል፡፡
በዘንባባ ምንጣፍ፣ በደመቀ እልልታ እና በበዛ አጀብ ከቤተ ፋጊ እየሩሳሌም የገባው መሲህ በቀራኒዮ አደባባይ ሲሰቀል ከወንጌላዊ ዮሐንስ በቀር ማንም ሊከተለው ጽናት አልነበረውም፡፡ ከተሰቀለው እውነት ጎን ለመቆም ቀርቶ አብሮ በአንድ መሶብ መቁረሱን ለመካድ እንኳ የዶሮ ጩኽትን የቀደመው ብዙ ነበር፡፡ ከመነሳት የበለጠ አሸናፊነት እንደሌለለ ትንሣኤው ህያው ምስክር ቢኾንም ስቅለቱ ግን እንክርዳዱን ከስንዴው ለማበጠር የቁርጥ ቀን ነበረችና አስፈሪ ኾና ታልፋለች፡፡ ከሐና እስከ ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ፤ ከጲላጦስ እስከ ሔሮድስ እየተመላለሰ እንዲንገላታ ተደርጓል፡፡
በመጨረሻም “ሁሉም ነገር ተፈጸመ” በማለት ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በራሱ ፈቃድ ለይቶ ራሱን ለሞት አሳልፎ ሰጠ፡፡ ዛሬ ክርስቲያኖች “አቤቱ ማረን፤ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜም አስበን” ሲሉ ቀኑን በስግደት ያሳልፋሉ፡፡
በታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/