ሽብርተኛው ትህነግ ሙሉ በሙሉ እስኪደመሰስ ከፀጥታ ኀይሉ ጎን በመሰለፍ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የፍላቂት ገረገራ ከተማ እናቶች ተናገሩ፡፡

0
90
ጥቅምት 08/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው እና ወራሪው የትህነግ ቡድን ወደ አማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ዘልቆ በመግባት መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመቶችን አድርሷል፤ እያደረሰም ነው፡፡ ሕጻናት እና እናቶች በግፍ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ለከፋ ሰብዓዊ ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ልጃገረዶች ተደፍረዋል፣ የአርሶ አደሩ ሰብል ማሳ ላይ ወድሟል፡፡ ወጣቶች እና ታዳጊዎች በተናጠል እና በቡድን በአሰቃቂ ሁኔታ ተጨፍጭፈዋል፡፡
ሽብርተኛው ትህነግ በደረሰባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን ዘርፏል፤ አውድሟል፡፡ የግለሰብ ድርጅቶች እና መኖሪያ ቤቶች መጠነ ሰፊ ምዝበራ እና ስርቆት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ በዚህም በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ለአስከፊ ጉዳት እና ስብራት ተጋልጠዋል፡፡ ይህንን ተከትሎም የፀጥታ ኀይሉ የሽብርተኛው ትነግን ወራሪ ቡድን እንቅስቃሴ በመግታት ተጨማሪ ጉዳት እና ውድመት ሳይደርስ ለመደምሰስ እየተሠራ ነው፡፡
የሽብር ቡድኑ ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ እስኪደመሰስ ከፀጥታ ኀይሉ ጋር በመሰለፍ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የፍላቂት ገረገራ ከተማ አስተዳደር እናቶች ተናግረዋል፡፡
አሸባሪው እና ወራሪው የትህነግ ቡድን ወደ አካባቢያቸው በወረረበት ወቅት በርካታ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ማድረሱን የገረገራ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አሳመነች አርዓያ ተናግረዋል፡፡ ሰዎች በግፍ ተገድለዋል፤ ሃብት እና ንብረት ተዘርፏል እንዲሁም ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ተዘርፈዋል ያሉት ወይዘሮ አሳመነች ቡድኑ ከተማዋን በኀይል ለቆ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኗል ብለዋል፡፡
በአካባቢው ያለው የፀጥታ ኀይል በሽብርተኛው ትህነግ ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ እየተፋለመ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ አሳመነች የከተማዋ ነዋሪ ኹሉን አቀፍ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡ የሽብር ቡድኑ ከአካባቢው ሙሉ በሙሉ እስኪጸዳም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የገለጹት፡፡
ወይዘሮ ሻሸወርቅ ንጉሤ በበኩላቸው የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ወደ አካባቢው ዘልቆ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ሰላም አግኝተው እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ የሽብርተኛው ትህነግን ለመደምሰስ ከሚደረገው የህልውና ዘመቻ ጎን በመሰለፍ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቁስለኞችን በመንከባከብ፣ ስንቅ እና ውኃ በማቅረብ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን የገለጹት ወይዘሮ ሻሸወርቅ ዘመቻው ሙሉ በሙሉ በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል፡፡
አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን ወደ ከተማዋ ዘልቆ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የንግድ ተቋማትን ዘርፏል፣ መኖሪያ ቤቶችን አውድሟል ያሉት ደግሞ ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ የትነበርሽ ብርሃኔ ናቸው፡፡ የሽብር ቡድኑ የኢትዮጵያውያን ኹሉ ስጋት በማይሆንበት ደረጃ መደምሰስ ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡
ዘመቻውን በአጭር ጊዜ እና በድል መቋጨት ይገባል ያሉት ወይዘሮ የትነበርሽ ለዚህም መላው ኢትዮጵያዊ ኹሉ ከፀጥታ ኀይሉ ጎን መሰለፍ ይገባዋል ነው ያሉት፡፡
እርሳቸው በሚኖሩበት አካባቢም ሴቶች ሠራዊቱን በስንቅ፣ በትጥቅ እና በሞራል እየደገፍን ነው ብለዋል፡፡ የሽብር ቡድኑን እኩይ ሴራ ለማምከንም በሁሉም አካባቢ ያለ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በጋራ በመቆም ዘመቻውን መደገፍ ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከመቄት
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ