አዲስ አበባ:መጋቢት 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጋር በመተባበር ዓለማቀፍ የሸማቾችን ቀን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሸማቾች መብት ጥበቃና ግንዛቤ ዴስክ ኀላፊ ሰይፉ አየለ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ሸማቾች በሕግ የተሰጣቸውን መብቶች ተረድተው መብቶቻቸውን ለማስጠበቅ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ለማስቻል ዓላማ ያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል ።
የሸማቾች ቀን በዓል መጋቢት 15 ቀን በየዓመቱ በዓለማቀፍ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ይካሄዳል፡፡ በዓሉ በሸማቾች መብቶች ላይ ግንዛቤን ለማሳደግ ዓላማ ያደረገ ዓለማቀፍ በዓል መሆኑን አቶ ሰይፉ አስረድተዋል።
ማንኛውም ሸማች መረጃ የማግኘት፣ አማርጦ የመግዛት፣ እንዲገዛ ያለመገደድ፣ በትህትና የመስተናገድ፣ ለደረሰበት ጉዳት ካሳ የመጠየቅና ከገዛው ዕቃ ላይ ጉድለት ሲያገኝ እንዲቀየርለት የመጠየቅ ሕጋዊ መብት እንዳለው ተገንዝቦ መብቱን ማስከበር እና የመብት ጥሰት ሲከሰት ለሕግ የማሳወቅ ተግባር እንዲፈጽም አስገንዝበዋል ።
ግብይትን በደረሰኝ መፈጸም ለሸማቾችም ሆነ ለነጋዴዎች ከሚሰጠው መተማመን ባሻገር ለመንግሥት ተገቢው ግብር እንዲደርስ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዳለውም ገልጸዋል።
በመድረኩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ አባላት እየተሳተፉ ነው።
ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!