ስድስት ሰዎች ሲያገግሙ ሁለት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ።

0
230

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 25/2012 ዓ.ም (አብመድ) ባለፉት 24 ሰዓታት ለ1 ሺህ 560 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ በሁለት ሰዎች ላይ የኮሮና ቫይረስ መገኘቱን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ በማኅበራዊ ገጹ እንዳስታወቀው ሁለቱም የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ አንደኛው ታማሚ ከባቱ (ዝዋይ) አዲስ አበባ ሄደው በሕክምና ተቋም ተኝተው ሕክምና ሲከታተሉ ናሙና ተወስዶላቸው የተመረመሩ የ49 ዓመት ወንድ ናቸው፡፡ ሁለተኛዋ ደግሞ በቤት ለቤት ቅኝትና አሰሳ የተገኙ የደቡብ ክልል ስልጤ ወረዳ ነዋሪ የ45 ዓመት ሴት ናቸው፡፡

የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ስድስት ተጨማሪ ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ አገግመዋል፤ ሁሉም ከድሬዳዋ መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከኮሮና ቫይረስ ያገገሙ ሰዎች ቁጥርም 75 ደርሷል፤ በሕክምና ክትትል ላይ የሚገኙት ደግሞ 55 ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ከመጋቢት 4/2012ዓ.ም ጀምሮ 135 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው በምርመራ ተረጋግጧል፤ የሦስት ታካሚዎች ሕይወት አልፏል፤ ሁለት የውጭ ዜጎች ደግሞ ወደ ሀገራቸው ተልከዋል፡፡ አጠቃላይ የተመረመሩት ሰዎች ብዛት ደግሞ 22 ሺህ 330 ደርሷል፡፡