ስለ ኮሮና ቫይረስ ዕለታዊ መረጃዎች

0
588

ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ 436 ሺህ 623 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፤ 111 ሺህ 856 ሰዎች ደግሞ ከሕመሙ አገግመዋል፤ 19 ሺህ 644 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡

• ሕንድ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ሰዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ተወስኗል፡፡ ሕንድ 492 የተረጋገጠ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች መኖራቸው ተረጋግጧል፤ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት አልፏል፤ ለ21 ቀናት ቤታቸው በመቆየት ደግሞ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ወስነዋል፡፡

• አንድ አራተኛው የዓለም ሕዝብ ዛሬ በቤት ውስጥ እያሳለፈ መሆኑ ተዘግቧል፡፡

• በእንግሊዝ ወደ 170 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ብሔራዊ በጎ ፈቃድ አግልግሎት ሊሰጡ ተዘጋጅተዋል፡፡

• የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፓርላማው የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁን እስከ ሚያዝያ 11 እንዲያራዝም ጠይቀዋል፡፡

• የኒው ዮርክ ገዥ የኮሮና ቫይረስ በፍጥነት እየተዛመተ እና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደግሞ ከሦስት ሳምንታት በኋላ አሜሪካ ወደ ቀድሞት እንቅስቃሴዋ እንደምትገባ ተናግረዋል፡፡

• አሜሪካ በኮሮና ቫይረስ አደጋ ላይ የወደቀውን ኢኮኖሚዋን እንዲያንሰራራ ለማድረግ የሁለት ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር በጀት አጽድቃለች፡፡ የጸደቀው በጀት የዕርዳታ ድርጅቶችን፣ የንግድ ተቋማትን እና የጤና ሥርዓቱን ለመደገፍ ይውላል። በአሜሪካ 55 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፤ 800 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

• ቻይና አዲስ በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠረ ዜጋ ሲገኝ ማንም ሰው መደበቅ እንደማይገባው መልእክት ተላልፏል፡፡

ቢቢሲ እና ሲ ኤን ኤንን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል፡፡

በአዳሙ ሽባባው