ስለ ቃፍታ ሁመራ በጥቂቱ

0
709
ስለ ቃፍታ ሁመራ በጥቂቱ
ባሕር ዳር፡ የካቲት 16/2013 ዓ.ም (አብመድ) ቃፍታ ሁመራና አካባቢው በውስጡ ልዩ ልዩ አዕዋፋት ዝርያዎችንና የዱር እንስሳትን የያዘ እጅግ ውብ መልከዓምድር ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት ደግሞ በሕገ ወጡ ትህነግ ተይዞ በአግባቡ ሳይለማ መቆየቱን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
የቃፍታ ሁመራ ብሔራዊ ፓርክና አካባቢው ከዚህ በፊት ትህነግ ባሰማራቸው ባለሃብቶችና አመራሮች በሕገወጥ መንገድ ተይዞ የቆየ መሆኑን በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ጊዜዊ አስተዳደር አስተዳዳሪ የአብሥራ እሸቴ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ደግሞ በቃፍታ ሁመራና አካባቢው የሚገኙ ጥብቅ ደኖችን፣ ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎችንና ማዕድናትን በተገቢ መንገድ ለማስተዳደር የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ የአብስራ ገለጻ ብሔራዊ ፓርኩ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ይገኛል፡፡ በፓርኩ ተከዜ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙ ዝሆኖች፣ አናብስት፣ ነብር ፣ የሜዳ ፍየል፣ የቆላ አጋዘን ፣ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው አዕዋፋት እና የዱር እንስሳት ይገኛሉ፡፡
በተለይም ለጉብኝት ወደ ቃፍታ ሁመራ ብሔራዊ ፓርክ ጎራ የሚሉ ጎብኚዎች ባለ ቀይ አንገት ሰጎንን በማየት ገራሚ ቆይታ ማሳለፍ እንደሚችሉ የአካባቢው ጊዜያዊ አስተዳደር ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ ፓርኩ ከጎረቤት ሀገር ኤርትራ ኮረብታማ ቦታዎች በቅርብ ርቀት የሚገኝ በመሆኑ ለዕይታ ማራኪ በመሆን ለጎብኚዎች፣ በዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሃብቶችና ግለሰቦች የሀብት ምንጭ መሆን ይችላልም ብለዋል፡፡
የህግ ማስከበር የህልውና ዘመቻን ተከትሎ የተገኘውን ዕድል ወደ ኢኮኖሚ በመቀየር ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት አቶ የአብሥራ የአካባቢውን ፀጋ በሚገባ በመጠቀም ዜጎች የልማቱ ተጠቃሚና ተሳታፊ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ በተለይም በአካባቢው የሚገኘውን ሠፋፊ የእርሻ ቦታ በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ከተቻለ በሀገር ኢኮኖሚ የበኩሉን ሚና ማበርክት እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ ፡- አዳሙ ሽባባው
ፎቶ- ከድረ ገጽ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ