“ሳንፈቅድ የተከፈተብንን የምንከላከለውን ጦርነት ዛሬ በሁሉም ግንባር ራሳችንን በመከላከል ተጨማሪ ቦታዎችና ንብረቶች እንዳይወሰዱ ማድረግ የሚያስችል ሥራ ተሠርቷል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

0
272

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 25/2013 ዓ.ም (አብመድ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶክተር) በህወሐት ውስጥ ባለ ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ ዛሬ በተወሰደው ሕግና ሥርዓት የማስከበር እርምጃ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ ብዙ የጦርነት ታሪኮች መለመዳቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም ለድህነት ምንጭ መሆኑን መንግሥትና ሕዝብ ይገነዘባል ብለዋል። በዚህም ባለፉት ጊዜያት ጦርነትን ለማስቀረት እልህ አስጨራሽ ትግል ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰዋል። ነገር ግን መንግሥት ያደረገው ጥረት ተስፋ በቆረጠው ቡድን ምክንያት ሳይሳካ መቅረቱን ገልጸዋል። ሁኔታው ጦርነት በቅን አሳቢዎች ፍላጎት ብቻ እንደማይቀር ያሳየ ነው በማለትም ገልጸውታል።

የጦርነቱ ዓላማ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት በማዳከም ለውጪ ጠላቶች አሳልፎ መስጠት እንደሆነም አብራርተዋል።

የትግራይ ሕዝብን ለዓመታት ሲጠብቀው በኖረው እና አሁንም ከብዙ ችግሮች እየታደገው ባለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ አሳፋሪና በታሪክ ውስጥ ጠባሳ የሚሆን ጥቃት እንደተሰነዘረበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

የጥፋት ቡድኑ ሰራዊቱ በዘር እንዲከፋፈልና እርስ በርሱ እንዲባላ ከማድረግ ጀምሮ እንቅስቃሴው እንዲገደብ ሲያደረግ እንደቆየም ተናግረዋል።

የትግራይ ሕዝብ ግን አብሮት ያለውን፣ ከአምበጣ መንጋ የተከላከለውን እና የሚያውቀውን ጦር ላለማስጠቃት አኩሪ ተግባር መፈጸሙን አብራርተዋል።

የትግራይ ሚሊሻና የልዩ ኃይል አባላት በወገኑ ላይ የሚከፈተው ጦርነትን ተገቢ አለመሆኑን በማመን ወደ ጎረቤት ክልሎች በመሸሽ ራሱን ለማግለል ጥረት ማድረጉንም አድንቀዋል። ተግባሩ መንግሥትን ያስደሰተ፣ ያስመሰገነና ቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው እንደሆነ አሳስበዋል።

የአማራ ሕዝብ፣ የአማራ ሚሊሻና የልዩ ኃይል አባላት በክልሉ ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን በመከላከል ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር ተቀናጅቶ አስፈላጊ ቦታዎችን መቆጣጠር እንደተቻለም ጠቅሰዋል።

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰጠው የሀሳብና የሞራል ድጋፍም መንግሥት በክብር የሚመለከተው እንደሆነ ተናግረዋል። በሁመራ፣ በዳንሻ እና በቅራቅር ውጊያዎች የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት የነበራቸው ተጋድሎ በታሪክ እንደሚዘከርም ገልጸዋል።

ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ውሎው ኢትዮጵያውያን የመከላከያ ሠራዊት አባላት ለመለዮአቸው፣ ለሰንደቅ አላማቸው፣ ለሀገራቸው እና ለሕዝባቸው የሚዋደቁ ጀግና ሠራዊት መሆናቸው የተረጋገጠበት እንደሆነም አስገንዝበዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ሕግና ሥርዓት የማስከበር ተግባሩን ለማጠናከር፣ እኩይ ተግባሩን ለማስቆምና የኢትዮጵያን ሠላምና አንድነት ለማስጠበቅ በማሰብ እንዲሁም ሠራዊቱን ለመደገፍ ማገልገል የሚችሉ ሦስት ስመጥር ሌፍተናንት ጀኔራሎችን ወደ ሠራዊቱ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል። ይህም ተቋሙን ፍጹም ኢትዮጵያዊ በማድረግ ሀገሪቱን የሚጠብቅና የሚከላከል ሠራዊት ለመገንባት ያስቻላል ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሳንፈቅድ የተከፈተብንን የምንከላከለውን ጦርነት ዛሬ በሁሉም ግንባር ራሳችንን በመከላከል ተጨማሪ ቦታዎችንና ንብረቶች እንዳይወሰዱ ማድረግ የሚያስችል ሥራ ተሠርቷል” ብለዋል። ይህም የጠላት ፍላጎት እንዳይሳካ ማድረጉንም ገልጸዋል።

የሠራዊት አባላቱ የጀመሩትን ተግባር በመተባበር አጠናክረው እንዲቀጥሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በሚቀጥሉት ቀናት የሚኖሩ የዘመቻ ሥራዎችን መንግሥት እንዳስፈላጊነቱ የሚገለጽ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ