ሰሜን ሸዋ ዞንን የልማት ቀጣና ለማድረግ እየተሠራ ነው።

0
278

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 18/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞንን የኢንቨስትመንት እና የልማት ሥራዎች በማሳደግ የልማት ቀጣና ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል አስታወቀ።

በሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃና ወደራ ወረዳ በአርሶ አደሮች በኩታ ገጠም መሬት የለማ 819 ሄክታር ሰብልን የፌዴራል እና የአማራ ክልል ባለስልጣናት ሰሞኑን በጎበኙበት ወቅት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ምክትል ሊቀ መንበር እና የማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለው እንደገለጹት በዞኑ የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር እና ኅብረተሰቡ ባደረገው ጥቂት ጥረት በርካታ ኢንቨስተሮችን የመሳብ ትልቅ ልምድ ታይቷል።

‹‹የተሟላ መልካም አስተዳደር ባይሰፍንም በተደረጉ ጥረቶች ግን የዞንና በየደረጃው ያለው አስተዳደር ከሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከውጭ አገራት ጭምር ባለሀብቶችን በመሳብ ላይ ይገኛል›› ያሉት አቶ ዮሐንስ ክልሉም የዞኑን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

‹‹አካባቢው ከክልሉ አልፎ ለሌሎችም የሚተርፍ ሀብት ይዟል፤ይህንን በአግባቡ ባለመጠቀም ችግር ውስጥ የምንገባባቸው ጊዜያት በርካታ ናቸው›› ያሉት አቶ ዮሐንስ ‹‹በሰሜን ሸዋ በኢንቨስትመንቱ ብቻ ሳይሆን በግብርና ምርታማነት እየታየ ያለውን ለውጥ እንደተስፋ በመቁጠር ለተሻለ ስኬት ጠንክረን መታገል ይኖርብናል›› ብለዋል።

በተለይ አርሶ አደሩ ከተደገፈ እና የተሻለ ትምህርት ከተሰጠው በግብርና ምርቱ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል የሞጃና ወደራ ወረዳ አርሶ አደር ማሳያ መሆኑንም አስታውቀዋል። ‹‹በዚህ ሳንኩራራ የአርሶ አደሩን የምርት ተሞክሮ ልምድ በማስፋፋት ሥራችንን እንቀጥላለን›› ማለታቸውን ኢ.ፕ.ድ ዘግቧል።

የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድማገኘሁ እንደገለጹት በኢንቨስትመንቱ መስክ ዞኑ ለበርካታ ኢንዱስትሪዎች የሚሆኑ ግብዓቶች የሚገኝበት ነው። የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀብት ምቹነት በመመልከት በርካታ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ፍቃድ እየወሰዱ ነው። በተለይም በዞኑ የሚገኙ ማዕድናትን የሚያለሙ ኢንቨስትሮች ኦፓል፣ ብረት እና የተለያዩ ማዕድናትን ለማውጣት ግንባታ ጀምረዋል።

‹‹ለኢንዱስትሪው መስክ የተመቸ ሠላማዊ ሁኔታ አለ›› ያሉት አቶ አቶ ተፈራ ከመካከለኛ እስከ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች በግንባታ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ይህንን የኢንቨስትመንት ዕድል በመጠቀም አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለኢንዱስትሪዎች በማቅረብ ራሳቸውንም ሆነ አገራቸውን ሊጠቅሙ እንደሚገባ አሳስበዋል።