“ሰላም የሚገነባው በሕዝብ ልብ ውስጥ ነው!” ርዕሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

365
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ

ባሕር ዳር፡ ጥር 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) “ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለብልጽግና ጉዟችን ስኬት!” በሚል መሪ ሐሳብ ከባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች ጋር ውይይት አካሒደዋል።

በውይይት መድረኩ የኢፌዴሪ ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ.ር)፣ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሣኅሉ (ዶ.ር) እንዲኹም ሌሎች የክልልና የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በመድረኩ ወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ኹኔታዎችን የዋጀ የመነሻ ሐሳብ ቀርቦ በውይይት ተሳታፊዎች ሃሳብና አስተያየት ተሰጥቶበታል።

ተሳታፊዎች ከፀጥታ፣ ከሌብነትና ብልሹ አሠራር፣ ከትምህርት ጥራት፣ ከሥራ አጥነትና ኑሮ ውድነት፣ ከአዲሱ የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ማስተር ፕላን፣ ከዘረኝነትና ከሃይማኖት ጉዳዮች ጋር የተያያዙና ሌሎች ክልላዊና ሀገራዊ ጉዳዮችን አንስተዋል።

በተነሱ ሐሳቦች ላይ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ አዲሱ የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ማስተር ፕላን የህዝብ ቅሬታ እንዳያስነሳ ሁሉንም ባሳተፈ መልኩ ጊዜ ተሰጥቶት ወይይት እንደተደረገበት ገልጸዋል።

ከንቲባው ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት አገልግሎት ለማግኘት የሚመጣ የከተማችን ነዋሪዎች መብቱን በገንዘብ መግዛት የለበትም ብለዋል። በአሠራር ሒደት የሚስተዋሉ ብልሹ አሠራሮችን በዘላቂነት መቅረፍ እንድንችል ኹሉም አካል ተሳታፊ መኾን እንዳለበት አስረድተዋል።

ዋናው ጉዳይ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ቢኾንም ተጠያቂነት ለማስፈን ግን የሁሉም የከተማችን ነዋሪዎች እገዛ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የኢፌዴሪ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ.ር) እንደገለፁት፤ በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች መነሻቸው ከውስጥም ከውጭም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚመኙ ኃይሎች እንደሚመነጩ ገልጸዋል።

ሸኔ የኢትዮጵያ ጠላት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሸኔ ባለበት አካባቢ በሰላም የሚኖር ሕዝብ የለም፤ ሲፈልግ ዘርን መሰረት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የፖለቲካ ውግንናውን መሰረት አድርጎ ንጹሐንን የሚጨፈጭፍ የሁላችንም ጠላት በመኾኑ በጋራ ልንተባበር ይገባል ብለዋል።

ሚኒስትሩ መፍትሔው መተባበር ነው፤ ከተከፋፈልን ለጠላቶቻችንም ኾነ ለሸኔ ምቹ ኹኔታን እንፈጥራለን። ኦሮሞና አማራ ወንድምና እህት ነበሩ፤ አሁንም ወንድምና እህት ናቸው፤ ወንድምና እህት እንደኾኑ ይቀጥላሉ፤ ካጠፋን እኛ እንጠፋለን እንጂ የኦሮሞና የአማራ ወንድማማችነት ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም ሲሉ አስረድተዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መሥዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በሰጡት ማጠቃለያ እንደሀገር የሚያዋጣን በብሔር አጥር ውስጥ ተነጣጥለን ሳይሆን ሚዛናዊ ሁነን በኢትዮጵያዊነት ስነልቦና በጋራ ስንቆም ነው ብለዋል።

በአብሮነት ስሜት በጋራ ካልተነሳን ሀገራዊ አንድነትን መገንባት አንችልም ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ፤ ጠንካራ ሀገር ለመገንባትና ሰላማችንን ለማረጋገጥ የአብሮነት እሴቶችን ማጠናከር ይኖርብናል።

የመንግሥት ቀዳሚው ሚና የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ ነው፤ ሰላም የሚገነባውም በሕዝብ ልብ ውስጥ ነው። መንግሥት የዜጎችን ሰላም ለማረጋገጥ በሚያደርገው ሒደት ሁሉም ሕዝብ ተሳታፊ መኾን እንዳለበት ገልጸዋል።

በጅምላ መፈራረጅ ችግሮቻችንን ያወሳስባል እንጂ ለውጥ አያመጣም፤ ሀገርንም አይገነባም፤ ሰላምን አያረጋገጥም። የሚዛናዊ የፖለቲካ ስርዓት ለመገንባት መቻቻልና መደማመጥ አለብን ብለዋል።

ዶ.ር ይልቃል፤ ወንድማማችነትና እህትማማችነት የሚገለጽበት መንገድ ብዙ በመኾኑ የእኛ መርህ መኾን አለበት፤ ተባብረን፣ ተደጋግፈንና ተደማምጠን ከሠራን ሀገራችንን ከችግር ማውጣት እንችላለን ማለታቸውን ከርእሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት የደረሰን መረጃ ያመላክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!