ሰላም እና ጤና ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች!

0
52

ባሕር ዳር: የካቲት 04/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የቆዳ ቀለም የማንነት መለኪያ ነበር፡፡ የሰው ልጅ በብቃቱ እና በማንነቱ ሳይሆን በቆዳ ቀለሙ አሳዳሪ እና ሎሌ፣ ባሪያ እና ጌታ፣ ምልዑ እና ጎደሎ ተብሎ ተፈርጆም ያውቃል፡፡ ጥቁሮች ከነጮች ጋር በአንድ አግዳሚ ወንበር ላይ መቀመጣቸው ነጮቹን እንደመናቅ፤ በአንድ አውቶብስ ውስጥ መሳፈራቸው ክብራቸውን እንደመገዳደር የሚቆጠርበትን ሁነት ዓለም በአንድ ወቅት አስተናግዳለች፡፡

ሌላው ቢቀር የጥቁሮች እና የነጮች በሚል የተለዩ የሃይማኖት ተቋማት መኖራቸው የችግሩን አሳሳቢነት እና አስከፊነት የሚያሳይ ነበር፡፡ ዓለማዊነት ቀርቶ መንፈሳዊነትን የሚሰብኩት ተቋማት በቆዳ ቀለም ልዩነት ፍጡራንን ለይተው እንዲመለከቱ ተደርጓል፡፡ ማመን እና በጎ መሥራት ሳይሆን ጥቁር ወይም ነጭ ሆኖ መፈጠር ለመመረጥ ምክንያት እንደሆነም የሚሰበክበት ጊዜ ነበር፡፡

ነጭ መሆን ሚዛን የሚደፋበት እና ጥቁር ሆኖ መፈጠር አንገት የሚያስደፋበት አስከፊ ጊዜ ትናንት በጥቁሮች የትግል መስዋእትነት ተቀይሯል፡፡ የትናንቶቹ ጥቋቁሮች ለልጆቻቸው መብት እና እኩልነት መከበር የከፈሉትን መራር ተጋድሎ ልጆቻቸው ሲሰሙ ምን እንደተሰማቸው መገመት አይከብድም፡፡ እርግጥ ነው ዛሬም አልፎ አልፎ የዚያ አስከፊ ስርዓት እና ጊዜ ዳፋ ፈጽሞ ጠፍቷል ማለት አይደለም፡፡

ከሃሪየት ቱብማን እስከ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር፣ ከማልኮም ኤክስ እስከ ሮዛ ፓርክስ እና ሌሎችም ጥቁር ፖለቲከኞችን፣ የማሕበረሰብ አንቂዎችን፣ ተራማጆችን እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ትግል ለመዘከር በየዓመቱ ወርሃ የካቲት “የጥቁሮች ታሪካዊ ወር” ተደርጎ ይከበራል፡፡ በተለይም የጥቁር ሕዝቦች የእጅ ሥራ ውጤት በሆነች አሜሪካ፣ ከ150 ዓመታት በላይ በዘር ፖለቲካ በታመሰችው ካናዳ እና ራሳቸውን የተለየ ዝርያ ያላቸው የዓለም ሕዝቦች አድርገው ይመለከቱ በነበሩት ጀርመኖች ዘንድ የጥቁሮች ታሪካዊ ወር በተለየ መልኩ እየተከበረ ያልፋል፡፡

የጥቁሮች ታሪካዊ ወር እንዲከበር ለመጀመሪያ ጊዜ ሃሳቡ የቀረበው በእውቁ የታሪክ ምሁር ካርተር ጂ ውድሰን አማካኝነት እንደ ምዕራባውያኑ የዘመን ስሌት በ1926 እንደነበር ይነገራል፡፡ ሃሳቡ የቀረበበት አመክንዮም የጥቁር ሕዝቦችን የነጻነት ተጋድሎ ታሪክ ለመዘከር እና አሜሪካ ለጥቁር አፍሪካዊያን ያላትን ክብር እንድታረጋግጥ ከማሰብ የመነጨ ነው የሚሉ አሉ፡፡

የካቲት የጥቁሮች ታሪካዊ ወር ሆኖ እንዲከበር የተመረጠበት ምክንያትም በተለይም በአሜሪካ ሁለት ዓበይት ክስተቶች ነበሩ፡፡ የመጀመሪያው ጉዳይ የ1863ቱ የነጻነት አዋጅ በፕሬዚዳንት አብርሃም ሊንከን የተፈረመው በወርሃ የካቲት በመሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ 16ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አብርሃም ሊንከን እና አፍሪካ-አሜሪካዊው አንደበተ ርቱዕ፣ የማሕበራዊ ለውጦች አቀንቃኙ፣ ጸሐፊው፣ ተራማጁ እና ተወዳጁ ፍሬዴሪክ ዳግላስ የተወለዱበትን ወርሃ የካቲትን ለመዘከር ያለመ እንደሆነ ይነገራል፡፡

“የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ የአሜሪካ ታሪክ ነው” የሚሉ የጥቁር ሕዝቦች ሰብዓዊ መብት ታጋዮች መበራከት እና መበርታት የኋላ ኋላ እየበረታ መጣ፡፡ የካርተር ጂ ውድሰን የጥቁሮች ታሪካዊ ወር ክብረ በዓልም ከግማሽ ምዕተ ዓመታት በኋላ በአሜሪካ ሕጋዊ እውቅና እና ሰውነት አገኘ፡፡ (እ.አ.አ) 1976 በፕሬዚዳንት ጄራልድ ፎርድ መሪነት ወርሃ የካቲት በአሜሪካ የጥቁሮች ታሪካዊ ወር መሆኑ እውቅና ተሰጠው፡፡

ላለፉት 46 ዓመታትም በዓለም ዙሪያ የካቲት የጥቁሮች ታሪካዊ ወር ሆኖ እንደተከበረ ቀጥሏል፡፡ በዘንድሮ ዓመትም “ሠላም እና ጤና ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች!” በሚል መሪ ሃሳብ የካቲት የጥቁር ሕዝቦች ታሪካዊ ወር ሆኖ ይታሰባል፡፡ ዓለም ከተዛነፈ የቆዳ ቀለም እይታዋ ሙሉ በሙሉ ተላቃለች ባይባል እንኳን ቢያንስ አስከፊ ከሆነ የቆዳ ቀለም ልዩነት ሰቆቃ እና መሸማቀቅ ነጻ የወጡ ጥቁሮች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው “እኔ ጥቁር ነኝ፤ ነገር ግን ውብ ነኝ” ማለት ችለዋል፡፡

የዘር ፖለቲካ ለሚንጣት የዛሬዋ ኢትዮጵያ ትምህርት እና ተሞክሮ የሚሆነው የጥቁሮች ታሪካዊ ወር አዲስ ዕይታ እና ተስፋ ለተስፋዋ ምድር ማሳየት እንደሚችል ነው፡፡
ምንጭ፡- አልጀዚራ እና ሮይተርስ

በታዘብ አራጋው

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/