ሰሃላ ሰየምት ወረዳን ከሰቆጣ የሚያገናኘው የተከዜ የብረት ድልድይ በመፍረሱ ለተደራራቢ ችግር መጋለጣቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ።

80
ባሕር ዳር :መጋቢት 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሃላ ሰየምት ወረዳን ከብሔረሰብ አሥተዳደር ዞኑ ዋና ከተማ ሰቆጣ የሚያገናኘው የተከዜ የብረት ድልድይ በመፍረሱ ለተደራራቢ ችግር መጋለጣቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። ድልድዩ በ2012 ዓ.ም ነሐሴ ላይ በጎርፍ ምክንያት በመፍረሱ ከአገልግሎት ውጭ ኾኗል። ድልድዩ ዛሬም ድረስ መልሶ ባለመገንባቱ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እያስከተለ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።
አሚኮ ያነጋገራቸው የሰሀላ ነዋሪ አቶ ብርሃኑ ሸጋው ድልድዩ በመሰበሩ ምክንያት ከብሔረሰብ ዞኑ ጋር ለመገናኘት ችግር እንደፈጠረ ተናግረዋል። በወረዳው ሆስፒታል ባለመኖሩ የጤና አገልግሎት የሚያገኙት ወደ ሰቆጣ እና ዝቋላ በመሄድ እንደነበር ገልጸዋል። በድልድዩ መሰበር ምክንያት ወላድ እናቶች ሳይቀር ለሕክምና ከ200 ኪሎ ሜትር በላይ ወደ ጎንደር እንደሚጓዙ ተናግረዋል። በዚህ ጉዞ ላይ የነብሰ ጡር እናቶች ሕይወት እያለፈ እንደኾነም ነግረውናል። ወደ ሰቆጣ ከተማ ገብቶ ዞናዊ ጉዳዮችን ለማስፈጸም በጎንደር በኩል ዞሮ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን መጓዝ እና ከፍተኛ የመጓጓዣ ወጭ መክፈልን እንደሚጠይቅም አመላክተዋል። በዚህም ጊዜያቸው ገንዘባቸውና ጉልበታቸው እንደሚባክን አስረድተዋል። ድልድዩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ ማኅበረሰቡ ከእንግልት መዳን አለበት ሲሉም አቶ ብርሃን ተናግረዋል።
ሌላው የሰሀላ ነዋሪ አቶ ካባው መንግስቱ ድልድዩ ከፈረሰ በኃላ መልሶ ባለመሠራቱ ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንግልት ተጋልጠናል ብለዋል። አቶ ካባው በንግድ ሥራ የሚተዳደሩ ሲኾን ከሰቆጣ ወደ ሰሀላ ተጓጉዘው ለመሥራት መቸገራቸውን ገልጸዋል። የድልድዩ አለመሰራት ወደ ወረዳው የሚገባ ሰብዓዊ የእርዳታ ቁሳቁስ ሲገኝ እንኳን በጊዜ እንዳይደርስ እንቅፋት በመኾን ነዋሪዎችን ለተደራራቢ ችግር እንዳጋለጣቸው ተናግረዋል።
ወደሰቆጣ ለመሻገር በተለይም በክረምት ወቅት ሞተር አልባ ጀልባ እንዳለ ጠቅሰው ለሰዎች ሕይወት ግን አስጊ ነው ብለዋል። የወንዙ ውኃ በክረምት ወቅት የሰዎችን ሕይዎት ጭምር እያጠፋ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት። አቶ ካባው ድልድዩ እንደገና ተገንብቶ ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጥም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የነዋሪዎችን ጥያቄ ለዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞን መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ አቅርበናል። መምሪያ ኀላፊው አቶ ሰሎሞን እሸቱ የድልድዩ መፍረስ በአካባቢው ላይ ከነበረው ጦርነት ጋር ተያይዞ ነዋሪዎችን ለኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንግልት በመዳረግ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ኾኖ እንደቆየ ተናግረዋል። እንደፈረሰ በፍጥነት ለመገንባት የታቀደ ቢኾንም በጦርነት ምክንያት እስካሁን ድረስ ሳይሠራ መቆየቱን ገልጸዋል። አቶ ሰሎሞን የድልድዩ መልሶ ግንባታ የ2015 ዓ.ም ክረምት ከመግባቱ በፊት እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት። ለሥራው የሚኾን የማሽን እና የሲሚንቶ አቅርቦት በብሔረሰብ ዞኑ የተዘጋጀ ሲኾን የብረት አቅርቦቱን ደግሞ የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር እንደሚሸፍን መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
ድልድዩ በፊት ከነበረበት መጠን በበለጠ ኹኔታ እንደሚገነባም ነግረውናል። እንደበፊቱ አይነት በውኃ የመዋጥ እና የመደርመስ አደጋ እንዳይገጥም ከመሬት ያለው ከፍታ ይጨምራል ተብሏል። በፊት የነበረው ርዝመት 90 ሜትር ሲኾን በአዲስ ሲሠራ ግን ወደ 140 ሜትር ከፍ እንደሚልም አቶ ሰሎሞን ጠቅሰዋል።
መምሪያ ኀላፊው የድልድዩ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ሁሉ ዝግጅት ተደርጎ ወደሥራ መገባቱን ገልጸዋል። የግንባታው ተቋራጭ የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት በሙሉ ትኩረት በመሥራት በአጭር ጊዜ አጠናቅቆ የማኅበረሰቡን ችግር እንዲፈታም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!