“ሦስት አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል” ትምህርት ቢሮ

0
83
ባሕር ዳር: ሕዳር 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ የክልሉን ትምህርት ቢሮ የ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኅላፊ ማተብ ታፈረ (ዶ.ር) የቢሮውን የሩብ ዓመት አፈጻጸም ለምክር ቤቱ ሲያቀርቡ በክልሉ ለሦስተኛ ዙር ተከፍቶ የነበረው ጦርነት እና ወረራ በመማር ማስተማር ሥርዓቱ እና በትምህርት ተቋማት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሮ አልፏል ብለዋል፡፡ በጦርነቱ 542 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ እና ከፊል ጉዳት ደርሶባቸዋል ያሉት ኅላፊው ጉዳቱን ለማካካስ የተጠናከረ ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡ ከጉዳቱ ሙሉ በሙሉ ለማገገም አሁንም የተጠናከረ ድጋፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ክልሉ በጦርነት ውስጥም ሆኖ ለትምህርት ስራው የተለየ ትኩረት በመስጠት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል ያሉት ዶክተር ማተብ 11 ትምህርት ቤቶች በአዲስ ተሰርተው ለአገልግሎት ሲውሉ በርካታ ጥገና የተደረጋላቸው ትምህርት ቤቶችም እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ “ሦስት አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል” ነው ያሉት ኅላፊው በሪፖርታቸው፡፡
የ2015 የትምህር ዘመን በንቅናቄ እንደተጀመረ ያነሱት ኅላፊው የአንድ ጀምበር የተማሪዎች ምዝገባ፣ የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ትውውቅ እና የትምህርት ማስጀመሪያ ቅድመ ዝግጅቶች ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርተዋል ብለዋል፡፡
የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ በቂ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ነበር ያሉት ኅላፊው ውስን ክፍተቶች ቢኖሩም በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል ብለዋል፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ የትምህርት ዘመኑን በንቅናቄ ጀምሮ ዓመቱን በሚዘልቅ ንቅናቄ ይቋጫል ያሉት ዶክተር ማተብ የትምህርት ጥራን ማረጋገጥ፣ የትምህርት ግብዓቶችን ማሟላት እና ለትምህር ባለድርሻ አካላት በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ላይ ግንዛቤ መፍጠር የቀጣይ ጊዜ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው ተብሏል፡፡
አካታች የትምህርት ሥርዓት መገንባት፣ ዲጂታል የትምህርት ሥርዓት መፍጠር እና የገበያውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የትምህርት ሥርዓት ማንበር ትኩረት ይሰጣቸዋል ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!