ምክር ቤቱ በትግራይ ክልል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፀደቀ።

0
239

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 26/2013 ዓ.ም (አብመድ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመደበኛ ስብሰባው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፀደቀ።
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው እለት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ እያካሄደ ይገኛል። በመደበኛ ስብሰባውም በኢፌዴሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመቀበልና ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ተመልክቷል። ምክር ቤቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላም አጽድቆታል።

የኢፌዴሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት በትናትናው እለት ባደረገው 21ኛ አስቸኳይ ልዩ ስብሰባ በትግራይ ብሔራዊ ክልል ውስጥ እየተፈፀሙ ያሉ ተግባራት ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚጥሱ ናቸው፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔዎችን ጭምር በመጣስ በርካታ ሕገ ወጥ ተግባራት እየተፈፀሙ ነው፤ ይህን ሁኔታ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱ ተጠቅሷል።

በሕገ መንግሥቱ በተደነገው መሠረት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ ልዩ እርምጃዎችን መውሰድ የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ እና ተግባራዊ በማድረግ ሁኔታውን በመቆጣጠር በሀገሪቱ ሠላምና ሕልውና ላይ የተጋረጠውን አደጋ መከላከል አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ፤ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93/1/ሀ መሰረት በትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለስድስት ወራት ተፈጻሚ የሚሆን ሲሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈፅም በኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሰብሳቢነት የሚመራና አግባብነት ካላቸው አካላት የተውጣጡ አባላት ያሉት ግብረኃይል በዚህ አዋጅ መቋቋሙም ተገልጿል።

ግብረኃይሉ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፤ ‘‘የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረሀይል’’ ተብሎ እንደሚጠራም ተነግሯል። አዋጁ በመላው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድር ተፈፃሚ የሚደረግ ነው፤ እንደ አስፈላጊነቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈፃሚ ወይም ቀሪ የሚሆንባቸውን ተጨማሪ አካባቢዎችን ግብረኃይሉ በሚያወጣው በመመሪያ ይወስናል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስመልክቶ ዝርዝር መረጃዎች በየጊዜው ለኅብረተሰቡ የሚሰጡ ይሆናል ተብሏል።
ምንጭ፡-የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here