‹‹ምርጫው ሰላማዊነቱን ጠብቆ ተጠናቅቋል›› የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ

0
132

‹‹ምርጫው ሰላማዊነቱን ጠብቆ ተጠናቅቋል›› የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ
ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሲካሄድ ውሏል፡፡ የምርጫ ሂደቱን በተመለከተ
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም የከፋ ችግር ከሌለ በስተቀር ሲሰጠው የዋለው የመራጮች ድምጽ ወደ ቆጠራ ይገባል፤ በምርጫ ጣብያ
የብርሃንና የጸጥታ ችግር ከሌለ የምርጫ ውጤት ይቆጠራል ነው ያሉት፡፡ ዛሬ ድምጽ ሲያሰጡ የዋሉ ጣቢያዎች ድምጽ
እንዲቆጥሩ እንደሚጠበቅና ትእዛዝ እንደተላለፈም ተናግረዋል።
ከምርጫ ጋር በተያያዘ የጸጥታ ችግር አላጋጠመንም ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ጥቃቅን የሚባሉ ችግሮች መፈጠራቸውንም ገልጸዋል፡፡
“ምርጫው ሰላማዊነቱን ጠብቆ ተጠናቅቋል” ያሉት ሰብሳቢዋ ከጥቃቅን ችግሮች ውጭ የጸጥታ ችግር አልገጠመንም ሲሉም
አረጋግጠዋል፡፡
በምርጫ ሂደቱ በሲዳማ ክልል የድምጽ መስጫ እጥረት በመከሰቱ በተደረገ ሥራ ለማደረስ ተሞክሯል ብለዋል፡፡ በአንዳንድ
የምርጫ ጣብያዎች ማዳረስ ባለመቻሉ አንዳንድ የምርጫ ጣብያዎች ላይ ሂደቱ መቋረጡንም አስታውቀዋል፡፡ በሲዳማ
በተቋረጡ የምርጫ ክልሎች ነገ ከአምስት ሰዓት ጀምሮ ምርጫ ይካሄዳል ነው ያሉት፡፡
በጋምቤላ ክልል በአንዳንድ የምርጫ ክልሎች ላይም ቁሳቁስ እጥረት በማጋጠሙ ምርጫው ቆሟል ብለዋል፡፡ የተቋረጡባቸው
አካባቢዎች ላይ የምርጫ ቁሳቁስ ጋምቤላ መድረሱንና ወደ አካባቢው ደርሶ መቼ ምርጫ እንደሚካሄድ የምናሳውቅ ይሆናልም
ብለዋል፡፡
በቤንሻንጉል ክልል አሶሳ አካባቢም የምርጫ ቁሳቁስ እጥረት ማጋጠሙንና ምርጫው መቋረጡን ነው የተናገሩት፡፡
በአማራና በደቡብ ክልሎች ከምርጫው ጋር በተያያዘ የቀረቡትን አቤቱታዎች አጣርተን ምላሽ እንደሚሰጡም ገልጸዋል፡፡
በመንግሥት በኩል አቤቱታዎቹ ውሸት መሆናቸውን መገለጻቸውንም ተናግረዋል፡፡ ምርጫው በአጠቃላይ ጥሩ የሚባል ውሎ
እንደነበረው ነው የተናገሩት፡፡
ምርጫው አሳታፊና ሰላማዊ እንደነበርም በመግለጫው ተነስቷል፡፡ በምርጫው የሀገር ውስጥና የውጭ ታዛቢዎች ሂደቱን
እንደተከታተሉ ነው የተነገረው፡፡
ከ44ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ ታዛቢዎች መሳተፋቸውም በመግለጫው ተነስቷል፡፡ ከ200 በላይ ታዛቢዎች ደግሞ ከውጭ
መምጣታቸው በመግለጫው ተመልክቷል፡፡
አነሰተኛ የሚመስሉ ነገር ግን መሻሻል የሚገባቸው ችግሮች መታዬታቸውም ተነስቷል፡፡ በምርጫ ሂደቱ በቀላሉ የማይፈታ ችግር
አለመግጠሙም ተነግሯል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m