“ምርታማነትን ስናስብ ጤናማ ዜጎችን ማፍራት ዋናው ትኩረታችን ሊሆን ይገባል” የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ

138
ደሴ:መጋቢት 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን ጤና መመሪያ አዘጋጅነት የትራኮማ በሽታን መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ዞናዊ ውይይት በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው። በውይይቱ የዞንና የሁሉም ወረዳዎች የሥራ ኀላፊዎች ተሳትፈውበታል።
በደቡብ ወሎ ዞን ከ13 ሺህ በላይ ወገኖች የዓይን ጭራ ወደ ውስጥ መቀልበስ ችግር ያለባቸው ሲሆን እነዚህን ወገኖች ከዚህ በሽታ ነጻ እንዲሆኑ ህክምና መስጠትና ሌሎች ወገኖች ደግሞ በትራኮማ በሽታ እንዳይጠቁ መከላከል በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።
ትራኮማ ከንጽህና ጉድለት ችግር የሚመጣ በሽታ በመሆኑ በተለይ የገጠሩ ማኅበረሰብ ደረጃውን የጠበቀ መጸዳጃ ቤት እንዲኖረው መስራት ተገቢ መሆኑም በውይይቱ ተነስቷል።
በደቡብ ወሎ ዞን ደረጃውን የጠበቀ መጸዳጃ ቤት የሚጠቀሙ የኅብረተሰብ ክፍሎች 22 በመቶ ብቻ በመሆናቸው ይህን አኀዝ ወደ 85 በመቶ ለማሳደግ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ይገባል ተብሏል።
በዞኑ በሽታን ለመከላከል ከተያዙ ቁልፍ ተግባራት መካከል የተሻሻሉ መጸዳጃ ቤቶችን በመገንባት በተለይ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ አቶ ጌታቸው በለጠ ተናግረዋል።
ምርታማነትን ስናስብ ጤናማ ዜጎችን ማፍራት ዋናው ትኩረታችን ሊሆን ይገባል ያሉት የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አብዱ ሁሴን ትራኮማን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት መደገፍና በባለቤትነት መስራት የሁሉም ዜጋ የወቅቱ ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመዋል።
ለጽዳትና ጤና አጠባበቅ ሥራዎች ትኩረት መስጠት ጤናማ ዜጋ ለማፍራት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባም በውይይቱ ተመላክቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!