ማንቸስተር ዩናይትድ ቸልሲን በማሸነፍ በካራባኦ ዋንጫ ጉዞው ቀጥሏል፡፡

0
191

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 20/2012 ዓ.ም (አብመድ) በእንግሊዝ የካራባኦ ዋንጫ ትናንት ምሽት ተጠባቂ ጨዋታዎች ተካሂደዋል፡፡ ቸልሲ ማቸስተር ዩናይትድን፣ ሊቨርፑል አርሰናልን በየሜዳቸው የጋበዙበት ጨዋታ ተጠባቂ ነበር፡፡

በምሽቱ ጨዋታ በፕሪሚዬር ሊጉ በአጣብቂኝ ጉዞ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ እንደሚሸነፍ የብዙዎቹ ግምት ነበር፤ ነገር ግን የሶልሻዬሩ ቡድን 2ለ1 ከሜዳው ውጭ አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል፡፡

የማንቸስተርን የማሸነፊያ ግቦች ራሽፎርድ በ25ኛው ደቂቃ በጨዋታና 73ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሯል፡፡ አሰልጣኝ ኦሊገናር ሶልሻዬር ‹‹ራሽፎርድ በፍጹም ቅጣት አመታቱ ክርስቲያኖ ሮናልዶን እየመሰለ መጥቷል›› ሲል አሞካሽቶታል፤ የቸልሲን ብቸኛ ግብ ባትሽዋይ በ61ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል፡፡
ሁለተኛው ተጠባቂ የሊቨርፑልና አርሰናል ጨዋታ 19 ግቦች መረብ ላይ አርፈውበት ተጠናቅቋል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 5ለ5 በሆነ ውጤት በማጠናቀቃቸው ወደ መለያ ምት አምርተዋል፡፡

በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ኦሪጂ ለሊቨርፑል እና ማርቲኔይል ለአርሰናል ሁለት ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል፡፡ ጨዋታው በተጀመረ ገና በ6ኛው ደቂቃ የአርሰናሉ ሙስጣፊ ኳስን በራሱ መረብ ላይ በማሳረፍ ነበር የግብ ናዳውን ያስጀመረው፡፡ ሊቨርፑል አንድ የፍጹም ቅጣት ምት አግኝቶ ሚልነር ወደ ግብ ቀይሯል፤ አርሰናሎች ደግሞ አምስቱንም ግብች በጨዋታ አስቆጥረዋል፡፡
ጨዋታው በመደበኛው ክፍለ ጊዜ 5ለ5 በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምት አምርተው ሊቨርፑል 5ለ4 አሸንፎ ወደ ሩብ ፍጻሜው ተቀላቅሏል፡፡

ሌላኛው የምሽቱ ጨዋታ አስቶንቪላ በሜዳው ከወልቨርሃምተን ወንደረርስ (ወልቭስ) የተገናኘበት ነበር፤ ጨዋታው በባለሜዳው 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቅቋል፡፡

በምሽቱ ጨዋታ በሊቨርፑልና አርሰናል መረብ ላይ ያረፉ ኳሶች ብዛትም 19 ሆኗል፤ በአጠቃላይ በምሽጹ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ 25 ኳሶች መረብ ላይ አርፈዋል፡፡

የሩብ ፍጻሜ ድልድሉ ዛሬ ከሰዓት በኋላ የሚታወቅ ይሆናል፡፡

ምንጭ፡- ቢቢሲ