ባሕርዳር: መጋቢት 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ክልላዊ የፀረ ሙስና አስተባባሪ ኮሚቴ ክልላዊ ጥምረት ለላቀ የሙስና ትግል በሚል መሪ ሀሳብ ምክክር እያደረገ ነው።
በአማራ ክልል የክልላዊ የፀረ ሙስና አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሰቢ ቢያዝን እንኳሆነ በምክክሩ ላይ እንደተናገሩት ክልሉ በለውጥ ሂደት ላይ ነው። በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ ግን በርካታ ለውጡን የሚያደናቅፉ ችግሮች ተከስተዋል ብለዋል።
ከነዚህ ችግሮች አንዱ ከጦርነት ያልተናነሰው ሙስና ስለመኾኑም ነው የገለጹት። ሙስና ያሰብነውን እንዳናሳካ፣ ካለምነው እንዳንደርስና አንድነታችን እንዳይጠናከር የሚያደርግ ከጦርነት ያልተናነሰ ፈተና ነው ብለዋል።
ሙስና የሰላም ትግሉን አደጋ ውስጥ የሚከት የመልካም አሥተዳደር ችግር እየፈጠረ በመንግሥት እና በሕዝቡ መካከል ሰላም እንዳይኖር የሚያደርግ እንቅፋት በመኾኑ በጋራ መመከት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።
የፍትሕ ተቋማት የፀረ ሙስና ትግሉን እንዴት ይደግፉት፣ እንዴት የሕዝቡን በሰላም የመኖር ጥያቄ ምላሽ ይስጡ የሚል ሀሳብ በምክክሩ ላይ ትኩረት የሚደረግበት ሃሳብ መኾኑንም አንስተዋል።
ሰብሰቢው ሙስናን በመታገል ሕጋዊነትን ማስፈን፣ ሕገወጥነትን መቆጣጠርና የሕግ የበላይነትን ማስፈን ከሁሉም የሚጠበቅ ጉዳይ ነው ብለዋል።
በክልል ደረጃ የተቋቋመው ኮሚቴ ከየዞኑ እና ከሌሎች ኮሚቴዎች ጋር በመቀናጀት ሥራዎችን በአግባቡ ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
በምክክሩ የምዕራብ አማራ ዞን አሥተዳዳሪዎች፣ የጂኦፖሊታንት ከተማ ከንቲባዎችና የምዕራብ አማራ ዞን የፀረ ሙስና አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት እየተሳተፉ ነው።
ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!