መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደውን ህግ የማስከበር እርምጃ መጠናቀቅን ተከትሎ በወቅቱ በአፋጣኝ የመልሶ ማቋቋም መርሀ ግብር በመንደፍ ወደተግባር መግባቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡

0
182
መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደውን ህግ የማስከበር እርምጃ መጠናቀቅን ተከትሎ በወቅቱ በአፋጣኝ የመልሶ ማቋቋም መርሀ ግብር በመንደፍ ወደተግባር መግባቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 03/2013 ዓ.ም (አብመድ) በቅርቡ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተፈናቀሉ ሰላማዊ ዜጎችን ለመደገፍ በዩናይትድ ኪንግደም ለሦስት ሳምንታት ሲካሄድ የቆየው የበየነ መረብ የገቢ ማሰባሰበያ ዝግጅት መጠናቀቂያ ላይ አቶ ደመቀ መኮንን እንደተናገሩት መንግስት ላለፉት ሁለት አመታት ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ሂደት ውስጥ መግባቱን አስታውሰው በሌላ በኩል መንግስት በፖለቲካ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚ ዘርፍ እያካሄደ ያለው ሪፎርም ባልተዋጠላቸው የውስጥና የውጭ አካላት ቅንብር በተገመደ ሴራ ህዝባችን ለችግርና ለጥፋት ሲዳረግ ቆይቷል፡፡
በቅርቡም በህወሓት ጁንታ የሰሜኑን የአገራችንን ክፍል ሉኣላዊነት በማስከበር ላይ በሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ በውድቅት ሌሊት የተፈፀመው ኢሰብኣዊ ድርጊት መላውን ህዝባችንን ያስቆጣ እኩይ ተግባር ነው፡፡
መንግስት ይህን ዘግናኝ ድርጊት በፈፀሙ የክህደት ሃይሎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የህግ ማስከበር እና አገርን የመታደግ ተግባር አከናውኗል ብለዋል፡፡በተደረገውም ሁለገብ ርብርብ ጁንታው ፈጽሞ በማያገግም መልኩ ግብአተ መሬቱ ተጠናቋል፤ ርዝራዦቹም በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ህግ የማስከበር ሂደት በሰሜኑ የአገራችን ክፍልና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ወገኖች በፀረ ሰላም ሀይሉ በተነዛው ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ እና ሆን ተብሎ በዚህ ሀይል በተፈጠሩ ግጭቶች ወገኖቻችን ከቤት ንብረተቸው ተፈናቅለዋል ለስደትም ተዳርገዋል ነው ያሉት፡፡
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በኤምባሲዎች አስተባባሪነት ወገኖችን ለመደገፍና ለማቋቋም የገንዘብ ማሰባሰብ ተግባር ላይ መግባታችሁ የሚያስመሰግን ብቻ ሳይሆን የተቀደሰም ተግባር ነው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
“በዩናይትድ ኪንግደም የምትገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለመከላከያ ሰራዊታችን ከዚህ ቀደም ካበረከታችሁት ከፍተኛ የገንዘብ እና የሀገር ወዳድነት ድጋፍ በተጨማሪ ተፈናቃይ ዜጎቻችንን ለማቋቋም ከኤምባሲያችን ጋር በትብብር እያደረጋችሁት ላለው ድጋፍ የማሰባስብ ተግባር በራሴና በመንግስታችን ስም አመሰግናለው” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል መንግስት ሁለገብ የሆነ የሪፎርም ሂደት ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምር ትኩረት ካደረገባቸው አበይት ጉዳዮች አንዱ ዜጋ ተኮር የሆነ ዲፕሎማሲ ሲሆን በውጭ የሚኖረው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ በሰላም፣ በልማት እንዲሁም በዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ዙሪያ የሚካሄደውን ርብርብ ለማሳካት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸውም አብራርተዋል፡፡
መንግስት ዳያስፖራው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሀገር ግንባታ ላይ እንዲሳተፍ የህግ ማእቀፍ ማሻሻያዎችና ተቋማት የማደራጀት ተግባራት ማከናወኑን ገልፀው፣ ዳያስፖራው በሰላም ግንባታ፣ በማህበራዊ ዘርፍ፣ በኢኮኖሚ፣ በባህልና በቱሪዝም በተናጠልም ሆነ በጋራ የሃገራችንን እድገትና ብልፅግና በመተባበር እንዲያፋጥን ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል ነው ያሉት፡፡
“ሪፎርሙን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ለመንግስት አስፈላጊ የሆነው የውጭ ምንዛሪ ችግርን ለመቅረፍ ገንዘብ በህጋዊ መንገድ ወደሀገር ውስጥ በመላክ የጥቁር ገበያን የገንዘብ ዝውውርን ለማምከን በሚደረገው ጥረትም የበኩላችሁን ሚና እንድትጫወቱ ጥሪ አቀርባለሁ” ብለዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ብርቱካን አያኖ እንደተናገሩት ደግሞ በዩናይትድ ኪንግደም ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ቀደም ሲል ሀገራቸውን ለመደገፍ የገንዘብ ፣ የእውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋልን፡፡ አሁንም የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት ለምታደርጉት የገንዘብ ማሰባሰብ ጥረት ምስጋና ለማቅረብ እወዳለሁ ብለዋል፡፡
ድጋፍ የማሰባሰብ ስራው በተቀናጀ መልኩ በሁሉም አቅጣጫ ተጠናክሮ ቀጥሏል ያሉት ደግሞ አቶ ምትኩ ካሳ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽነር ናቸው፡፡ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በቂ ልምድ ያለን በመሆኑ በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡
የዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላም ዳዊት በበኩላቸው የዳያስፖራውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ እንዲቻል መንግስት የዳያስፖራ ኤጀንሲ በማቋቋም ከሴክተር ተቋማት ጋር በመቀናጀት የዳያስፖራውን ተሳትፎ የማሳደግ ስራ በትኩረት በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ዳያስፖራው የሀገሩን እድገት እና ብልፅግና ለማፋጠን የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ዳያስፖራው ሪፎርሙን በመደገፍ ከኤምባሲው ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ እንደሚቻል ገልጸው በሀገራችን ብሄራዊ ጥቅሞች ዙሪያ የዛሬውን የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ጨምሮ በህዳሴ ግድብ የገንዘብ ድጋፍ የማድረግ ፣ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ለቀረበው ጥሪ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት በገንዘብ እና በህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ሲፈፀም በቁጭት በመነሳሳት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰው ኤምባሲው ከዳያስፖራው ጋር በቀጣይ ተጠናክሮ የሚሰራቸውን ጉዳዮች አመላክተዋል፡፡
የኢትዮጵያዊያን ግብረሀይል በዩናይትድ ኪንግደም አስተባባሪ አቶ ዘላለም ተሰማ እንደተናገሩት የተጀመረውን ሪፎርም በመደገፍ አቅም በፈቀደ መጠን የሚያስፈልገውን ድጋፍ ሁሉ በማድረግ አገርን የመደገፉ ሂደት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን መግለፃቸውን በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኢምባሲ የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here