አዲስ አበባ: ግንቦት 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ ባለው እጥረትና የዋጋ ንረት ምክንያት መንግሥት ምርቱን ለማቅረብና በተሻለ ዋጋ ተደራሽ ለማድረግ “የፍራንኮ ቫሉታ” አሠራርን ዘርግቷል። “ፍራንኮ ቫሉታ” አንድን ምርት በሙሉ ወይንም በከፊል ከቀረጥ ነፃ ኾኖ እንዲገባ ዕድል የሚሰጥ አሠራር ነው።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር “በፍራንኮ ቫሉታ” የንግድ አሠራሩ እየተሳተፉ ያሉ ነጋዴዎች ጋር ውይይት እያደረገ ነው። በውይይቱ በኢትዮጵያ በተለይም ስኳር፣ ሩዝ፣ የሕጻናት ወተት፣ ዘይት እና የስንዴ ዱቄት በዚሁ አሠራር ወደ ሀገር እንዲገቡ መደረጉ ተነስቷል። ምንም እንኳን እነዚህ ምርቶች “በፍራንኮ ቫሉታ” መግባት ቢችሉም ዋጋቸው ግን እስካሁን አልቀነሰም ነው የተባለው።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በልሁ እንደ ሀገር 411 አስመጭዎች የተሳተፉበት ይህ የንግድ ዘርፍ በመሰረታዊ ፍጆታዎቹ ላይ መንግሥት የትርፍ መጠን ገደብ ያስቀመጠ ቢኾንም ዋጋው ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መጥቷል ብለዋል፡፡
የሱፍ ባለ 5 ሊትር ዘይት ከውጭ ከ 335 እስከ 422 ብር (እስከ 6 ነጥብ 1 ዶላር) ተገዝቶ እንዲገባ እየተደረገ ነው። ኾኖም አሁን ገበያ ላይ ያለው ዋጋ በችርቻሮ ከ800 እስከ 1ሺህ ብር ኾኗል ተብሏል። በማሳያነት ይህ ተነሳ እንጂ በበርካታ ምርቶች የሚታየው የዋጋ ንረት ተመሳሳይ እንደኾነ ነው የተገለጸው። በዚህ “የፍራንኮ ቫሉታ” ሂደት ባለፈው የበጀት ዓመት 10 ወራት መንግሥት ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ቢያጣበትም የታሰበውን ዓላማ ማሳካት ግን አለመቻሉ ነው በመድረኩ የተብራራው።
በመድረኩ የተሳተፉ ነጋዴዎች የዶላር እጥረት፣ ምርቶቹን የሚገዙባቸው ሀገራትና በኢትዮጵያ ያለው የዶላር የምንዛሬ መጠን የሰፋ ልዩነት መኖር ኪሳራ ውስጥ እንደከተታቸው ተናግረዋል።
መንግሥት የዶላር አቅርቦት ችግርን ከፈታ የተፈቀዱትን የንግድ ምርቶች አስገብተው በበቂ መጠንና በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ማድረግ እንደሚችሉም ነጋዴዎቹ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው አባቡ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!