‹‹መሬቱን እንጅ እናንተን አንፈልጋችሁም ተብለናል›› እስረኞች
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 02/2013 ዓ.ም (አብመድ) በማንነታቸው እና በፖለቲካ ልዩነታቸው የታሰሩ እና ሊረሸኑ የነበሩ 64 እስረኞች በመከላከያ ሰራዊት ነፃ ወጥተዋል፡፡
በሕጋዊ መንገድ የማንነት ጥያቄ ያነሱ አማራዎች በትግራይ ክልል የተለያዩ ማጎሪያ ቦታዎች ታስረው እንደነበር በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል፡፡ መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደውን ሕግ የማስከበር ርምጃ ተከትሎም ወራሪው፣ ተስፋፊውና አሸባሪው ትህነግ 15 ሺህ 800 እስረኞችን ወደተንቤን ዓቢ ዐዲ የምድር ውስጥ ማጎሪያ ቤቶች አሽሽቷቸውም ነበር፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ ሕግ የማስከበሩ ርምጃ እየጠነከረ መምጣቱን ተከትሎ ሕገ ወጡ ቡድን መውጫ መግቢያ ሲያጣ በማንነታቸው እና በፖለቲካ ልዩነታቸው ለእስር የተዳረጉ 64 ሰዎች ለግድያ ተለይተው ሌሎቹ ከእስር ተለቀቁ፡፡
ለግድያ የተዘጋጁት 64 የማንነት እና የፖለቲካ እስረኞችም ወራሪው፣ ተስፋፊውና አሸባሪው ትህነግ በመከላከያ ሰራዊት በደረሰበት ጥቃት ከለቀቃቸው በኋላ በሰራዊቱ ታጅበው መቀሌ ሲገቡ አነጋግረናቸዋል፡፡
የወልቃይት ነዋሪ የሆነው እና የማንነት ጥያቄ በማንሳቱ ብቻ ለ14 ዓመታት በእስር የተሰቃየው ስማቸው ተካልኝ የሞት ፍርድ ተበይኖበት እንደነበር ነግሮናል፡፡ ጥፋቴ ያለውን ሲነግረንም የወልቃይት አማራዎች እየተፈናቀሉ በሰፈራ ስም ከሌሎች አካባቢዎች ለመጡ ሰፋሪዎች ሰፋፊ መሬት መሰጠቱን መቃዎሙ ነበር፡፡ በእስር ቤት ውስጥ በእርሱ እና መሰል ጓደኞቹ በርካታ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ይፈፀም ነበር ያለው ስማቸው ከምንም በላይ የሚያመው ግን ሊያስወግዱት የፈለጉትን ሰው ሰበብ ፈጥረው ለብቻው ካሰሩ በኋላ ገድለው ራሱን አጠፋ ብለው የሚያስወሩት ነገር ነበር ይላል፡፡
ከሁለት ዓመታት ከስድስት ወራት በፊት ሃገራዊ ለውጡን ተከትሎ የራያ ጥሙጋ አካባቢ ተወላጆች የማንነት ጥያቄያችን ይከበር በሚል በግልፅ አደባባይ ወጥተው ነበር፡፡ በወቅቱ ከ54 በላይ ተወላጆች በህገ ወጡ ቡድን በተተኮሰ ጥይት ሲጎዶ በርካቶች ደግሞ ወደቆቦ ሸሽተው ጊዜ አሳልፈዋል፡፡ ‹‹መሬቱን እንጅ እናንተን አንፈልጋችሁም ተብለናል›› የሚለው ብርሃኑ በላይ ተፈራ በወቅቱ በትህነግ ከሚፈለጉ የመብት ጠያቂዎች እና የትውልድ ቀየውን ለቀው ከሸሹት መካከል አንዱ ነበር፡፡ ከሦስት ወራት በኋላ አገር አማን ሆኗል ብሎ ወደቀየው መመለሱን ተከትሎ በምሽት ከቤቱ ታፍኖ ተወሰደ፡፡
ብርሃኑ በህገ ወጡ የትህነግ ቡድን ከታፈነ በኋላ በቀድሞው የጣሊያን ምሽግ አምባላጌ የጀመረው እስር ከአምባለጌ እስከ መሆኒ፤ ከማይጨው እስከ ባዶ ስድስት፤ ከመቀሌ እስከ ዓቢ አዲ ያላንከራተቱበት ማረሚያ ቤት ያላስተናገደው ግፍና መከራ የለም፡፡ እነብርሃኑ የመጨረሻ የሞት ቀነ ቀጠሮ ተቆርጦላቸው ሕዳር 23/2013 ዓ.ም ለግድያ ወደ ተንቤን ገዛ ተጋሩ እንደወሰዷቸውም ይናገራል፡፡ ነገር ግን የተንቤን ማረሚያ ቤት ኃላፊ ባለቀ ስዓት በእነዚህ ሰዎች ደም እጃችን አናጨቀይም ማለቱን ተከትሎ በገዳዮች መካከል ልዩነት ተፈጠረ፡፡ በዚህ ውዝግብ መካከል ነበር የሰማይ ጀቶች የምድር ኮማንዶዎች ወደ አካባቢው መቃረባቸው የተሰማው፡፡
የመንግስት ህግ አስከባሪዎች ወደቦታው መቃረባቸውን ተከትሎም የሕገ ወጡ ቡድን አባላት እግሬ አውጭኝ ብለው አካባቢውን ሲለቁም ለሞት የተዘጋጁት ንጹሃን የነጻነት ብርሃን ወጣላቸው፡፡ የሃገር መከላከያ ሰራዊትም አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረግ መቀሌ እንዳደረሳቸው ነግረውናል፡፡
እስረኞቹ ህይዎታቸውን ለታደጋቸው እና አስፈላጊውን እንክብካቤ ላደረገላቸው የመከላከያ ሃይል ምስጋና አቅርበው ለዘመናት የታገሉለት ዓላማ ዳር እንዲደርስ አሁንም ከመንግስት ጎን በመሆን እንደሚታገሉ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – መቀሌ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ