ሕግ የማስከበርና የሕዝቡን ሠላም መጠበቅ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አስታውቀዋል፡፡

0
74

ባሕር ዳር፡ መስከረም 20/213ዓ.ም (አብመድ) የፌዴራል ፖሊስ “ከራስ በላይ ለሕዝብ እና ለሀገር ክብር” በሚል መሪ ሐሳብ ወታደራዊ ትርዒት አሳይቷል፡፡

በትርዒቱ መልእክት ያስተላለፉት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው ጣሰው የፌዴራል ፖሊስ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ድጋፍ ያልተደረገለት፣ በተለያዩ ጊዜያት መጠነኛ ማሻሻያ እየተደረገለት ለሕዝብ አግልግሎት ሲሰጥ የቆየ ተቋም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በተቋሙ ግልፅነት አግልግሎት አሰጣጥ ላይ ቅሬታ ሲቀርብበት እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡ ይህንን መነሻ በማድርግም ባለፉት ሁለት ዓመታት የፖሊስ አግልግሎት የሚፈልገውን ፈረጀ ብዙ ጉዳዮች በተለመደው አካሄድ መምራት ስለማይቻል የተለያዩ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደኮሚሽነሩ መግለጫ ችግሮች ተለይተው ወደ ሥራ ተገብቷል፤ በጥናት ተመሥርቶም በአምስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ሪፎር ተደርጓል፤ የተቋሙ የሰው ኃይል ግንባታ በአስተሳሰብና በክህሎት አንድነት ሊያመጡ በሚችሉ ሥራዎች ተጀምረው ውጤት እያስመዘገቡ ነው፤ የተቋሙን አሠራር እና አደረጃጀት በማስተካከል ግልፀኝነት የሚታይበት አሠራርም ተዘርግቷል፡፡ ሠራዊቱ በመላ ሀገሪቱ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት የሚያስችል ቁሳቁስም ለማሟላት በተከታታይ እየተሠራ ነው፤ ተቋሙ መታጠቅ የሚገባውን የቴክኖሎጂ መረጣ እና ማሻሻያ ተሠርቶ ወደ ተግባር ተገብቷል፤ እንደሀገር በተዘጋጀው የፖሊስ ቁመና እና መስፈርት መሠረት ወደ ሙሉ ትግበራ ለማስገባት ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡

እንደ ሀገር የተሰጠውን ተልዕኮ ለመፈፀም የፖሊስ ሠራዊቱን አመራር እና አባላት “ከራስ በላይ ለሕዝብ እና ለሀገር ክብር” በሚለው የለውጥ መመሪያ ሕዝቡን እና ሕገ መንግሥትን በመጠበቅ በተሰማራበት መስክ ሁሉ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ የአካል እና የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ሕዝቡን በታማኝንት እያገለገለ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በተቋሙ የተጀመረውን ለውጥ በየጊዜው በመፈተሽ ጥንካሬን በማጎልበት ጉድለትን በማረም የተጀመረው ዘመን ተሻጋሪ እና ዘመናዊ የፖሊስ ግንባታ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚከጥልም ኮሚሽነር ጄኔራሉ አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት የዲሞክራሲ ምኅዳር በመስፋቱ ከሀገራችው ተሰደው የነበሩት ወደ ሀገር እንዲገቡ መደረጉን እና የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸውንም ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል፤ መንግሥት ለሁሉም ጉዳዮች ግልፅ የሆነበት፣ የፖሊስ እና ፀጥታ አካላት ሪፎርም የተሠራበት ዘመን እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

“ሆኖም መነሻቸው የተለያዩ የሆኑ ችግሮች በተለያዩ አካላት ተፈፅመዋል፤ በቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን መንግሥት እና የፀጥታ አካላት በሠሩት ሥራ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል” ብለዋል፡፡ በቀጣይም “በእነዚህ ቀን እንደዚህ ይደረጋል” የሚሉ ፕሮፖጋንዳዎች በምንም መልኩ ተቀባይነት እንደሌላቸውና ሕግ የማስከበር እና የሕዝቡን ሠላም መጠበቅ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡

በአዳሙ ሺባባው

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here