ሕጋዊ እውቅና ተሰጥቷቸው የመኖሪያ ቤት ቦታ ሲጠባበቁ ለቆዩ ማኅበራት የቤት መሥሪያ ቦታ ለመስጠት ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

0
963
ሕጋዊ እውቅና ተሰጥቷቸው የመኖሪያ ቤት ቦታ ሲጠባበቁ ለቆዩ ማኅበራት የቤት መሥሪያ ቦታ ለመስጠት ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታን በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ መግለጫዉን የሰጡት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሣኅሉ (ዶ.ር) በጢስ ዓባይ ከተማ ለ1 ሺህ 49 አባላትን ላቀፉ 48 ማኅበራት የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ ከንቲባው በዘጌ ከተማ 1 ሺህ 261 አባላትን ላቀፉ 52 ማኅበራት ቦታ መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡ በመሸንቲ ከተማ ደግሞ ለ3 ሺህ 806 አባላትን ለያዙ 185 ማኅበራት 256 ሄክታር ቦታ ተዘጋጅቷል፤ እንዲሁም በዘንዘልማ አካባቢ 12 ሺህ 688 አባላትን ለያዙ 598 ማኅበራት 431 ሄክታር መሬት መለየቱን ተናግረዋል፡፡
የቦታ ልየታው ተከናውኖ የካሳ ስሌቱም እየተጠናቀቀ መሆኑን ዶክተር ድረስ አስረድተዋል፡፡ “በመሬት ላይ ያለ ሀብት ሁሉ ተለቅሞ የካሳው ስሌት በአካባቢ ጥበቃና መሬት አስተዳደር መምሪያ በኩል እየተሠራ ነው” ብለዋል፡፡ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከካሳ ስሌቱ ጎን ለጎን የመሬት ልማት አስተዳደር ባለሙያዎች የሽንሸና እና የብሎኪንግ ሥራን እያከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በኮምፒዩተር ላይ ያለው ሥራ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝና በመሬት ላይ ያለው ሥራ ደግሞ ቀጣይ ሳምንት እንደሚጀመር ነው ዶክተር ድረስ የገለጹት፡፡ “ሽንሸናው መሬት ላይ ተሠርቶ፣ ብሎክ ታስሮ ከተጠናቀቀ በኋላ ቦታ ከመሰጠቱ በፊት ማኅበራት 10 በመቶ በዝግ አካውንት እንዲቆጥቡ ይደረጋል” ብለዋል፡፡
በተያዘለት ዕቅድ መሠረት ይህ ሥራ ግንቦት 30 ይከናወናል ብለዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ ለባለፉት ስድስት ወራት የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ጥያቄን ለመመለስ አቅሙን ሙሉ ተጠቅሞ ሲሠራ መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡
የአርሶ አደሮችን ጥቅም በማስከበር በኩልም ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡
“አንዳንድ ግለሰቦች 200 ብር ካላዋጣችሁ ከማኅበር ትሰረዛላችሁ ብለው የሚለቁት መረጃ ለከተማ አስተዳደሩ ደርሷል፤ ይህ ፈጽሞ የተሳሳተ መረጃ ስለሆነ ኅብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፤ አርሶ አደሮች በተለየው የመኖሪ ቤት ቦታ ላይ እየዘሩ ነው የሚለውም ስህተት ነው” ብለዋል፡፡ ዘር እንዳይዘራ ከተማ አስተዳደሩ የጸጥታ አካላትን በመመደብ ጥበቃ እያደረገ መሆኑን ዶክተር ድረስ ጠቁመዋል፡፡
150 ካሬ ሜትር እንደሚሰጥ ያስታወሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እቅዳቸው ለሁሉም ማኅበራት ቦታን መስጠት እንደሆነና ለዚህም በትኩረት እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በየወቅቱ ማኅበራት ተደራጅተው ቦታ ሲሰጥ በመቆየቱ ከፍተኛ የሆነ የቦታ መጣበብ ስለተፈጠረ ሌሎች የቤት ማልሚያ አማራጮችን ማሰብ የግድ ስለሆነ ከተማ አስተዳደሩ ጥናት እያካሄደ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ጥናቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የሚወሰን ይሆናል እንጂ ነዋሪዎች በአፓርታማም ሆነ በጋራ መኖሪያ ቤት ምዝገባ እንዲካሄድ ከተማ አስተዳደሩ አቅጣጫ እንዳልሰጠ አሳስበዋል፡፡ የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቦታ ችግር መፍትሔ ለመስጠት ክልሉም የበኩሉን እገዛ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here