ሕዝብ ላነሳቸው ጥያቄዎች መንግሥት ምላሽ እንዲሰጥ እና አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠየቀ፡፡

0
127
ሕዝብ ላነሳቸው ጥያቄዎች መንግሥት ምላሽ እንዲሰጥ እና አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠየቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አማራን ትኩረት ያደረገ ግድያ፣ መፈናቀል እና የንብረት መውደም ለበርካታ ጊዜያት ተከስቷል፡፡ በቅርቡ ደግሞ በሰሜን ሸዋ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በፅንፈኞች በተፈጠረ ጥቃት የንፁሃን ሕይዎት አልፏል፣ ከተሞች ፈርሰዋል፣ ንብረት ወድሟል እንዲሁም ከጥቃት የተረፉት ደግሞ ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው ለእንግልት ተዳርገዋል፡፡
ይህንን ተከትሎ ከሰሞኑ በአማራ ክልል በርካታ ከተሞች ጥቃቶቹን በማውገዝ እና መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት እንዲያስጠብቅ የሚጠይቁ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡ በሰልፎቹም አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ፣ መንግሥት የሕግ የበላይነትን እንዲያስከበር እና የዜጎችን ደኅንነት እንዲያስጠብቅ ተጠይቋል፡፡
ዛሬ ደግሞ የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል፡፡ ጥንታዊ የሀገረ መንግሥት ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ በቅርቡ ለተደጋጋሚ ጊዜ “መንግሥት የሌለ በሚመስል መልኩ” በንፁሃን ላይ ጥቃቶች ተፈፅመዋል ያለው መግለጫው በተፈጠረው ችግር ዙሪያ የተሟላ መረጃ ለሕዝብ ተደራሽ አለመሆኑንም ጠቅሷል፡፡
የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋት ጉባኤ በመግለጫው እንዳለው ችግሮቹ እንዳይፈጠሩ ቀድሞ መሥራት በየደረጃው ያለው የመንግሥት መዋቅር መደበኛ ሥራ መሆኑን አመላክቷል፡፡ መንግሥት የዜጎችን ደሕንነት ማስጠበቅ ይኖርበታል ያለው መግለጫው ስድስት የአቋም መግለጫዎችንም አውጥቷል፡፡
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ ጊዜ በተፈፀመው የንፁሃን ጥቃት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው በመግለፅ ለሟቾች ነብስ እና ለተጎጂ ቤተሰቦች መፅናናት እንዲሆን እንፀልያለን ነው ያለው፡፡
በተለያየ ጊዜ ዜጎች በመኖሪያ ቀያቸው ተረጋግተው እንዳይኖሩ በተፈጠሩ ጥቃቶች እጃቸው ያለበትን እና ኅላፊነታቸውን ያልተወጡ የመንግሥት አካላት ሊጠየቁ ይገባል ብሏል፡፡
ጉዳት ለደረሰባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ከጉዳታቸው እንዲያገግሙ መንግሥት፣ ሕዝቡ እና የሃይማኖት ተቋማት ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ነው መግለጫው ያመላከተው፡፡ በንፁሃን ላይ በተደጋጋሚ የደረሱት ጥቃቶች ያመማቸው ወጣቶች እና የክልሉ ሕዝብ በሰላማዊ መንገድ ለመንግሥት ጥያቄውን አቅርቧል፤ በዚህም የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ክብር አለው ያለው መግለጫው አልፎ አልፎ የተስተዋሉ ችግሮች ግን ሕዝብን የሚወክሉ አይደሉም ብሏል፡፡
መንግሥት ከዚህ በኋላ መሰል ጥቃቶች እንዳይፈጠሩ የዜጎችን ደኅንነት የማስጠበቅ ግዴታ አለበት ያለው መግለጫው ሕዝቡም አካባቢውን ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበት አሳስቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በመላው ሀገሪቱ የተጀመረው ፆለተ ምህላ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በመግለጫው ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here