ሕዝቡ የተገነባበትን የባህላዊ፣ የዘመናዊ እርቅና የሰላም ተቋማትን በማጠናከር ሀገርና ሕዝብን ማዳን እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

0
279

ሕዝቡ የተገነባበትን የባህላዊ፣ የዘመናዊ እርቅና የሰላም ተቋማትን በማጠናከር ሀገርና ሕዝብን ማዳን እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 21/2013 ዓ.ም (አብመድ) በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት አማካኝነት በየወሩ የሚዘጋጀው አዲስ ወግ
አንድ ጉዳይ በምርጫ ወቅት ሰላምን ለማስፈን የሚረዱ ሀገር በቀል እውቀቶች እና የዘመናዊ ተቋማት ሚና በሚል አቢይ ጉዳይ
መክሯል። በውይይቱም ዘመናዊ ተቋማትና ባህላዊ እሴቶች ለሰላም ግንባታ ያላቸውን ሚና በተመለከተ በማኀበራዊ ሳይንስ
ምሁራን ቀርቧል፡፡
ሰላም እንዲፈጠር ሀገር በቀል እውቀቶችንና ተቋማትን መገንባትና ማጠናከር ይገባል፤ ባህላዊ የሽምግልና ሥርዓቶች ግጭቶችን
የሚያደርቁ መሆናቸውን ማመን እና ደግፎ ሥራ ላይ ማዋል ይገባልም ብለዋል ምሁራኑ። ግጭትን በዘላቂነት ለመፍታት
የሚያስችሉ ዘመናትን የተሻገሩ የእርቅና የሰላም እሴቶች መኖር ለሀገሪቱ ትልቅ እድል መሆናቸውን መገንዘብ እንደሚገባም
አብራርተዋል፡፡
የሕግ ብዝሃነት በኢትዮጵያ ቢኖርም ጥቅም ላይ አለመዋሉን ነው ምሁራኑ የገለጹት። ለዚህም የሀመሮችን “ኦሽ “ የተሰኘ
የሽምግልና እና የእርቅ ሥርዓት በምሳሌነት አንስተው ተቋማዊ ማድረግ ላይ ግን አለመስራቱ ችግሮችን የመፍቻ ቁልፉን አርቆታል
ብለዋል፡፡
ባህላዊ እሴቶች ለሀገር ግንባታ ሚና እንዲኖራቸው ለማድረግ መሥራት ይጠይቃል፤ ባህላዊ ተቋማት ለሰላም ግንባታ ያላቸውን
ሚና መፈተሸ እና በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ ያሉትን ባህላዊ ሀብቶችን በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ተሰናስነው ሊሰጡ
እንደሚገባም ምሁራኑ አንስተዋል፡፡
ባህላዊ እሴቶችና ተቋማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ባለቤት በመሆን መደገፍ ከተቻለ ችግሮችን ለመፍታት ግማሽ መንገድ
እንደመምጣት ነው፤ በመሆኑም ከወዲሁ ሊሰራባቸው እንደሚገባ የማኀበራዊ ሳይንስ ምሁራኑ ጠቁመዋል፡፡
የማኀበራዊ ሳይንስ ምሁሩ እና የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ የራስወርቅ አድማሴ (ዶክተር) ዘመናዊ ተቋማት
በሰላም ግንባታ ዙሪያ የላቸውን ሚና በተመለከተ ምልከታቸውን እና ምሁራዊ አስተያየታቸውን አጋርተዋል፡፡ መደበኛ ተቋማት
ሰላምን በማስፈን በኩል ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
የጋራ የሆኑ መደበኛ ተቋማት በዋናነት በዚህ ምርጫ ሊከሰቱ የሚችሉ ግጭቶችን ለመፍታት ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚገባም
ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ያለው ፉክክር ሰላማዊ እንዲሆን ተቋማት ኀላፊነታቸውን ሊወጡ
ይገባል ብለዋል፡፡
በምርጫ ወቅት ታዛቢዎች ሁሉንም ያካተቱ ቢሆን፤ የፓርቲዎችን የጋራ ኮሚቴ ማዋቀር ቢቻል፤ የሲቪል ተቋማት ሚናን ማሳደግና
የመንግሥት ሚናን ባግባቡና በጊዜው የመወጣት ኀላፊነት ቢያድግ የተሻለ ውጤት እንደሚመጣ ጠቅሰዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎችም ባህላዊና ዘመናዊ የሰላም እና የእርቅ ተቋማትን ዓላማቸውን ተገንዝቦ በጥናት ተደግፎ መጠቀም
እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡
በሀገሪቱ የወረደውን የአስተሳሰብ ልህቀት ለመመለስ የነበሩ መልካም እሴቶችን ማጠናከር፤ እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶችን እና
ያለመግባባት ቁርሾዎችን ለይቶ ማከም ይገባል ነው ያሉት፡፡
ዶክተር የራስወርቅ ፓርቲወች፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የሲቪክ ተቋማት በመናበብ በጋራ መሥራት ቢችሉና ተቀባይነት የሌላቸው
ተቋማት ከወዲሁ ሚናቸውን እንዲለዮ ቢደረግ መልካም መሆኑን መክረዋል፡፡ ሰላምን ከሥነ ምግባር ጋር የማቆራኘት ሥራ
በመሥራት በኩልም ተቋማት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንም ሁሉም የድርሻውን መወጣት
እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ጋሻው ፈንታሁን – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m