“ሕዝቡ አሁንም የሽብር ቡድኑን ለመደምሰስ ዝግጁ ይሁን” የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ

0
360

አዲስ አበባ፡ ጥር 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሕዝቡ በከፋፋይ ሐሳቦች ሳይረበሽ የትህነግ የሽብር ቡድንን በጋራ ለመደምሰስ ራሱን ማዘጋጀት እንዳለበት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ።

ርእሰ መሥተዳድሩ በክልሉ የደረሰውን ውድመት ሲዘግቡ ለቆዩ የመገናኛ ብዙኀን ሙያተኞች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ከአሁናዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች አኳያ ጥያቄዎች ተነስተውላቸዋል። ❝አሁን ላይ ከአሸባሪው ትህነግ አባላት የእስር መፈታት ጋር ተያይዞ ሕዝቡ ሁኔታው ቢያስቆጣው ትክክል ነው ፤ እውነትም አለው፤ የቡድኑ አባላትም ወንጀለኝነታቸውን እናምናለን❞ ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ አባላት ከታሰሩም በኋላ የቡድኑ ወረራ ተባብሶ የቀጠለና አሁንም ድረስ ለዳግም ወረራ እየተዘጋጀ በመሆኑ የአባላቱ መለቀቅና መታሰር ያለውን ሁኔታ ጋር ሲታይ የሽብር ቡድኑን ከመደምሰስ ዋና ዓላማ የሚያነጥል ጭንቀት ውስጥ የሚከት እንዳልሆነ ገልፀዋል።

ምንም እንኳን ሕዝቡ ከሀገራዊ አንድነትና ሰላም ፍላጎት አኳያ የቡድኑ አባላት መፈታት ቢያሰጋውም በተለይም የችግሩ ገፈት ቀማሽ የአማራ ሕዝብ በርካታ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ ከጀመረው ሽብር ቡድኑን የማጥፋትና ኅልውናውን የማረጋገጥ ዘመቻ መዘናጋት የለበትም ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።

ቡድኑ እየወጋን ያለው ብቻውን አይደለም በተለይም ከቅማንት ጽንፈኛ ቡድን፣ ከጉምዝና ሸኔ ቡድኖች እንዲሁም ከውጭ እንደ ግብጽና ሌሎች አንዳንድ ሃገራት ጋር በመሆን ኢትዮጵያ እንዳትለማ ለማድረግና ለማውደም እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ የሽብር ቡድኑ ካልተወገደ እንደ አማራ ሕዝብም ይሁን እንደ ኢትዮጵያ ትልቅ ስጋት በመሆኑ የክልሉ መንግሥት ከፌደራል መንግሥት ጋር በመነጋገር ሽብር ቡድኑ በሚጠፋበትና የወደመው ሃብት በሚተካበት ልክ ይሠራል ብለዋል። ሆኖም ሕዝቡ በሚነሱ አንዳንድ ሐሳቦች ተበርዞ ሽብር ቡድኑን ከመደምሰስ ዐቢይ ዓላማው እንዳይነጠል አሳስበዋል።

ዘጋቢ:–እንዳልካቸው አባቡ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/