“ሕወሓቶች እንዳይገድሉን ፈርተን በግዳጅ ወደ ጦርነት እየተማገድን ነው” ለመከላከያ ሠራዊት እጅ የሰጡ ሕጻናት ወታደሮች

0
142

“ሕወሓቶች እንዳይገድሉን ፈርተን በግዳጅ ወደ ጦርነት እየተማገድን ነው” ለመከላከያ ሠራዊት እጅ የሰጡ ሕጻናት ወታደሮች

ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) “ሕወሓቶች እንዳይገድሉን ፈርተን በግዳጅ ወደ ጦርነት እየተማገድን ነው” ሲሉ በሀገር መከላከያ የተያዙ ሕጻናት ወታደሮች ተናገሩ።

ከታዳጊ ሕጻናት ወታደሮች መካከል ኢየሩሳሌም ሃይላይ አንዷ ናት፤ እየሩሳሌም ሐምሌ 7/2013 ዓ.ም ከመቀሌ በድንገት ከቤቷ እንደወጣች ታፍና ወደ ጦርነት መምጣቷን ትናገራለች።

ምንም ዓይነት ሥልጠናም ሆነ መሣሪያ ሳታገኝ ”አሸንፈን አዲስ አበባ እንገባለን” በሚል ባዶ የተስፋ ቃል እየሸነገሉ ወደ ጦርነት እንዳስገቧቸውም ትገልጻለች።

በመጨረሻም ጦርነቱ ሲጀመር እንደ የዕድሜ እኩዮቿ ህጻናት “ደንግጠን ራሳችንን ለማዳን ለመከላከያ ሠራዊት እጃችንን ሰጥተናል” ትላለች ኢየሩሳሌም።

ሌላዋ ሕጻን ሄለን ሀድጉ በበኩሏ ከመቀሌ በመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ መሥመር አቅጣጫ አምጥተው አፋር ክልል እስከሚገቡ ድረስ ወዴት እየወሰዷቸው እንደሆነ ሳታውቅ መቆየቷን ታስታውሳለች።

በጦርነት ውስጥ ደረቅ ብስኩትና የወንዝ ውኃ እየጠጡ መቆየታቸውን የምትናገረው ሄለን፣ “ጓደኞቼ ራሳቸዉን ለማትረፍ በጭንቅ ላይ በነበሩበት ወቅት በሀገር መከላከያ ተማርኬ ሕይወቴ በመትረፉ ተደስቼያለሁ” ብላለች።

የትግራይ ሕዝብ የሕወሓት አሸባሪ ቡድን ራሱን በሥልጣን ላይ ለማቆየት ሕጻናትን በግፍ ወደ ጦርነት በመማገድ እየፈጸመ ያለውን ግፍ እንዲያቆምና እንዲታገለውም ጠይቃለች።

ሌላው ሕጻን ኢሳያስ ዓለም በበኩሉ ጁንታዉ የትግራይ ሕጻናትን በግዳጅ ወደ ጦርነት እየማገዳቸው መሆኑን ይመሰክራል።

እሱን ጨምሮ ሌሎች የእድሜ እኩዮቹ ተምረው ነገ የተሻለ ዜጋ ለመሆን ፍላጎትና ህልማቸው ቢሆንም፤ ጁንታው እንዳይገላቸው በመፍራት በተዋጊነት መሰለፋቸውን ይናገራል።

በጁንታው ተገድደው ወደጦርነት የገቡትና በመከላከያ ሠራዊት ጥንቃቄ የተሞላበት ርምጃ ህይወታቸው ተርፎ የተማረኩት ሕፃናት “የጁንታው አመራሮች የራሳቸዉን ልጆች በውጭ አገር እያስተማሩ የእነሱና የቤተሰቦቻቸው ሕይወት ተስፋ በመደብዘዙ ተቆጭተናል” ይላሉ።

ሕፃናቱ፣ የትግራይ ሕዝብ ራሱን በሥልጣን ለማቆየት ሲል ሕጻናትን በግፍ ወደ ጦርነት የሚማግደውን አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ሊታገለው እንደሚገባ ነው በአፋር ግንባር ለሀገር መከላከያ ሠራዊት እጅ የሰጡ ሕጻናት ወታደሮች የገለጹት።

ጁንታዉ በኢትዮጵያ ላይ በጀመረዉ አጥፍቶ መጥፋት ዘመቻ፣ የትግራይ ሕጻናትና ሴቶችን በተዋጊነት መጠቀም ከጀመረ ሰነባብቷል።

የሰሞኑን በአፋር ክልል ፈንቲ-ረሱ ዞን በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በከፈተዉ ጥቃት የተማረኩት እነዚሁ ህጻናት፣ የጁንታው አሳፋሪና ከሰብዓዊነት የወጣ ባህሪን ዓለም በትኩረት ሊያየው እንደሚገባም ተናግረዋል።

የአፋር ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር መሐመድ አሕመድ እንደገለጹት ጁንታው በዞኑ ያደረገዉን ወረራ የአፋር አርብቶ አደር ከመከላከያ ሠራዊትና ልዩ ኃይል ጎን በመቆም እየደመሰሰዉ ነዉ ።

ጁንታዉ ዛሬ በሀገር ላይ የከፈተዉ ጥቃት የቆየ ሀገር የማፍረስ ህልሙን እውን ለማድረግ በግልጽ የጀመረው መሆኑን ገልጸዋል።

“በጦርነቱም ሕጻናትን በሃሺሽ አስክሮ በማስገባት በተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ኾኖ ከማንም በላይ የትግራይ እናቶችና ሕጻናት ጠላትነቱን እያስመሰከረ ነዉ”ብለዋል።

በመሆኑም የትግራይ ሕዝብ ራሱን ለማቆየት ሕጻናትን በጭካኔ ወደ ጦርነት እየማገደ ያለውን አሸባሪ ቡድን፣ ከመከላከያና ከሌላዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን በመቆም እንዲታገለው ጠይቀዋል።

አሸባሪው ሕወሓት ሕጻናትን እያስገደደ ለሦስት ቀናት ያልበለጠ ሥልጠና በመስጠት ወደ ውጊያ አስገብቶ መቋቋም በማይችሉት ጦርነት እየማገዳቸው መሆኑን መከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ ገልጿል።

“በጦር ሜዳ ካሰለፋቸው ህጻናት ድል አገኛለሁ ብሎ በማሰብ እያስጨረሳቸው ይገኛል” ያለው ሚኒስቴሩ፤ ይህ ሳይበቃ በውጊያ የተገደሉትን ሕጻናት ሬሳ በመሰብሰብ “የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት ገደላቸው” ብሎ በውጊያ ያስጨረሳቸውን ሕጻናት ሬሳ መነገጃ ለማድረግ የተለመደውን የቅጥፈት ፕሮፓጋንዳ በማሰራጨት ሬሳቸውን ኹሓ ላይ ሰብስቦ እንደሚገኝ ጠቁሟል። ኢዜአ እንደዘገበው።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here