“ሕልውናችንን በደማችን እንዳረጋገጥን ሁሉ የሰላም ስምምነቱም ተፈጻሚ እንዲኾን ቁርጠኛ ነን” የሰሜን ጎንደር ዞን

63
ደባርቅ: ሕዳር 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ከትግራይ ክልል ጋር የተከዜ ተፋሰስን ተከትሎ ከ400 ኪሎ ሜትር በላይ በሚረዝም ድንበር ይገናኛል። በዚኽም ግንኙነቱ በተለይም ለ27 ዓመታት የሚደርስበትን በደል በሆደ ሰፊነት እየቻለ እና ጠንካራ እና ፍትሐዊ የትግል መስመር ይዞ እየታገለ ቆይቷል። የዞኑ ሕዝብ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ከተፈጸመ ጀምሮ ከሁለት ዓመታት በላይ በጦርነት ውስጥ ቆይቷል። የአካባቢው ሕዝብ ሕልውናውን ለማረጋገጥ በጦር ግንባር ከመሰለፍ ጀምሮ ስንቅና ትጥቅ በማቀበልም የደጀንነት ተግባሩን በአግባቡ ተወጥቷል። በተከፈለው መስዋእትነትም አካባቢውን ብሎም ሀገርን ከጠላት ነፃ በማውጣት የሰላም አየር መተንፈስ ችሏል።
መንግሥት ባሳየው ቁርጠኛ የሰላም ስምምነትም የሰሜን ጎንደር ዞን ሕዝብ ትልቅ የሰላም ተስፋን ይዟል። የተፈናቀሉት ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል። በጦርነት የፈረሱ መሰረተ ልማቶችን መልሶ የመገንባት ሥራው በቂ ነው ባይባልም ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።
የዞኑን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ የሰሜን ጎንደር ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኀላፊ ደጀን ግርማው ከአሚኮ ጋር ቆይታ አድርገዋል። መምሪያ ኀላፊው አሁን ላይ በዞኑ አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን ነው የተናገሩት። የዞኑ ሕዝብ ለሀገር ሰላም ቅድሚያ የሚሰጥ በመኾኑ መደበኛ የልማት ሥራውን ወደጎን በመተው አካባቢውን ከጠላት ወረራ ሲከላከል መቆየቱንም አቶ ደጀን ገልጸዋል።
ዞኑ ጠላት ከመሸገባቸው የተከዜ ተፋሰስ ሁሉም አካባቢዎች የሚዋሰን በመኾኑ በጦርነቱ ብዙ ዋጋ መክፈሉን ገልጸዋል። መንግሥት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ከተፈረጀው ህወሓት ጋር የወሰደው የሰላም ስምምነት በዞኑ ሕዝብ በኩል ተቀባይነት ያለው ነው ሲሉም አቶ ደጀን ገልጸዋል። የተደረገው የሰላም ስምምነት ለዞኑ፣ ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ዘላቂ መረጋጋት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረውም ገልጸዋል።
የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲኾን የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል መምሪያ ኀላፊው።
አቶ ደጀን በዞኑ ጠላት ለረጅም ጊዜ የቆየባቸውን አካባቢዎች መልሶ የመገንባትና የማደራጀት ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል። ይሁን እንጅ በአካባቢው አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ሰፊ ሥራን ይጠይቃል ነው ያሉት።
አቶ ደጀን የተከዜ ተፋሰስን ተከትሎ በተለይም በዞኑ ምሥራቅ ጠለምት አዋሳኝ አካባቢዎች የተደበቀ ሰላም ጠል ቡድን አልፎ አልፎ እንደሚስተዋል ተናግረዋል። ሰላምን ምርጫቸው ያደረጉት ግን ትጥቃቸውን እየጣሉ ከማኅበረሰቡ ጋር እየተቀላቀሉ መኾኑን ጠቁመዋል። የሰላም አማራጩን ለማደናቀፍ የሚሠሩ አካላትን ጠንካራ በኾነ ስምሪት በመቆጣጠር ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር እየተሠራ ነው። ለዚህም ውስጣዊ አደረጃጀትና አንድነትን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።
የሰሜን ጎንደር ሕዝብ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ተከባብሮ በሰላም መኖርና መሥራት የሚችል ሕዝብ ሥለመኾኑም አቶ ደጀን ገልጸዋል። ሰላም ወዳድ የኾነው የትግራይ ሕዝብ ሁሉ የሰላም አማራጩን እንደገዥ ሀሳብ መቀበል እንደሚገባው መልዕክት አስተላልፈዋል።
እንደ ሰሜን ጎንደር ሕዝብ “ሕልውናችንን በደማችን እንዳረጋገጥን ሁሉ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ተፈጻሚ እንዲኾንም ቁርጠኛ ነን” ሲሉም ተናግረዋል። ማንኛውንም ዓይነት አለመግባባት በሕግ እና በሥርዓት መፍታት ይገባል ነው ያሉት።
አቶ ደጀን የሕዝብን ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት የሚያስጠብቅ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!