ልጆች መልካም ሥራ እና ምግባር እንዲኖራቸው ማስተማር እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች አሳሰቡ፡፡

0
91

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ልጆቻቸው ሰማያዊውን ዓለም የሚያሳይ ምድራዊ ተግባር እና ምግባር እንዲኖራቸው ተግተው መሥራት እንዳለባቸው አብመድ ያነጋገራቸው የደሴ ከተማ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ፡፡

“በሰማይ የሚጸድቅ በምድር ያስታውቃል” ይላሉ አባቶች ሲመክሩና ሲዘክሩ፡፡ ሠላም፣ ፍቅር እና መተሳሰብ ዋጋቸው ሰማያዊ ቢሆንም እንኳን ምድራዊ ሐሴት እንዳላቸው ሁሉም ሃይማኖቶች በየአስተምህሮዎቻቸው ይሰብካሉ፡፡ የድሮዋ ወይራ አምባ፣ የመካከለኛ ዘመኗ ላኮመልዛ እና የአሁኗ ደሴ ከተማ ከግርማ ሞገሷ የጦሳ ተራራ ባሻገር ገዝፎ የሚነገርላት ታሪኳ የፍቅር ከተማ ስለመሆኗ ነው፡፡ ደሴ ከተማ ውስጥ እንኳን የሰው ልጅ ግዑዙ ታክሲ እንኳን “ታክሲዋ” እየተባለ በፍቅር ይጠራል፡፡

ደሴ ዕድሜ ጠገብ፣ ስመ ገናና እና ዋነኛ የንግድ እንቅስቃሴ ማዕከል ከመሆኗ ባሻገር የሃይማኖት እና የማንነት ስብጥር መልካም መስተጋብር ጎልቶ የሚስተናገድባት ከተማ እንደሆነች ይነገራል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ይህንን ነባር የአብሮነት እሴት የሚሸረሽር የሠላም እጦት አልፎ አልፎ እንደሚከሰት ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

“የደሴ ሕዝብ ለዘመናት የዘለቀው በፍቅር ነው” ያሉን የከተማዋ ነዋሪ አደም አሊ ሕዝቡ ደስታ እና መከራን ካለልዩነት አብሮ እንደሚጋራ ተናግረዋል፡፡ ካለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት ወዲህ ግን ይህን አብሮነት የሚሸረሽሩ የተለያየ መልክ ያላቸው ግጭቶች ማስተዋላቸውን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ከጊዜ ወደ ጊዜ የነዋሪዎቿ ቁጥር የጨመረባት ከተማዋ የቀደመውን እሴቶቿን ያልተረዱ ሰዎች እየበዙባት መሆኑ ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በተለይም ለግጭት ምክንያት የሆነው የሥራ ዕድል ፈጠራ በበቂ ሁኔታ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ግጭት ማኅበራዊ ክስተት መሆኑንና እንኳን የሰው ልጅ ጉልቻ እንኳን አብሮ ሲኖር ከመጋጨት እንደማይመለስ የተናገሩት የሀገር ሽማግሌው ሻምበል መስፍን ገብረማርያም በነባራዊ ሕይወት የሚያጋጥሙ ግጭቶች እያደጉና እየበዙ መሄድ እንደሌለባቸው መክረዋል፡፡ “ግጭት ቢፈጠር እንኳን ከአንድ ቡጢ በላይ ደሴ ማስተናገድ አይሆንላትም፡፡ የማስታረቅ እሴታችን እና የማሸማገል ባህላችን ፈፅሞ ባይጠፋ እንኳን ቀስ በቀስ እየደበዘዘ የመጣ ይመስላል” ብለዋል ሻምበል መስፍን፡፡ “የሰው መጤ የለውም፤ የአስተሳሰብ መጤነት ግን ይስተዋላል” ያሉት የሀገር ሽማግሌው የቀደመውን እሴት ለመመለስ እና ደሴ የምትታወቅበትን የመቻቻል ከተማነት ዳግም ለማጉላት በየእድሮች ሳይቀር እየተሠራ መሆኑን ነግረውናል፡፡

ሁሉም ሃይማኖቶች የሚያስተምሩት ፍቅርን፣ ሠላምን እና መተሳሰብ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የደሴ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጸሐፊ ቄስ መስፍን ጌታሁን ናቸው፡፡ በርካታ የእምነት ተቋማት፣ የበዙ የሃይማኖት አባቶች ባሉባት እና ሽበት በሚከበርባት ደሴ ከተማ ውስጥ “የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ልጆቻቸው ሰማያዊውን ዓለም የሚያሳይ ምድራዊ ሥራ እና ምግባር እንዲኖራቸው በርትተው ማስተማር ይኖርባቸዋል” ብለዋል፡፡

ሃይማኖትንና ማንነትን ሽፋን ያደረጉ ግጭቶች አልፎ አልፎ ሲከሰቱ እንደሚስተዋሉ አስተያየት ሰጪው ተናግረዋል፡፡ “ነዋሪዎችና መንግሥት ችግር ሲፈጠር ችግሩን ለመፍታት ከመጣደፍ ይልቅ ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት ቅድመ መከላከል ላይ ሊሠራ ይገባል” ብለዋል፡፡ “መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው ሲባል መንግሥት በማምለክ ነፃነታችን ጣልቃ አይገባም ማለት እንጂ በደኅንነት ስጋቶቻችን ላይ ገብቶ አይሠራም ማለት አይደለም” ብለዋል ቄስ መስፍን ጌታሁን፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የፀጥታ አካላት እና ወጣቶች ከመንግሥት ጋር በመተባበር ለከተማዋ ሠላም እንዲሠሩም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

የደሴ ከተማ አቀፍ እድሮች ከተለያዩ ሃይማኖቶች እና ከተለያየ የኑሮ ደረጃ ካላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ናቸው፡፡ አባላቱ ከማኅበረሰባዊ እሴት እና ከከተማዋ ሠላም ጋር በሚጣረሱ ተግባራት ውስጥ ተሳታፊ ሆነው ሲገኙ ከእድር አባልነት እስከ ማገድ የደረሰ የእርምት ርምጃ እንደሚወስዱ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው- ከደሴ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here