“ልዩ ኀይሉ አሸባሪውን ቡድን እየደመሠሠ ወደፊት እየገሰገሰ ነው” የአማራ ልዩ ኀይል አባላት

0
297
ሰሜን ወሎ ኮኪት: ጳጉሜን 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ልዩ ኀይል አሸባሪውንና ወራሪውን የትህነግ ቡድን በወረረበት አካባቢ እንዲቀበርና ድራሹ እንዲጠፋ በማድረግ ከፍተኛ ሚናን ተጫውቷል፤ እየተጫወተም ይገኛል።
የአማራ ልዩ ኃይል በላይ ዘለቀ ብርጌድ አባል የሆነው አዲስ ፈንታው ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሆን ግዴታውን በብቃት እየተወጣ እንደሆነ ተናግሯል።
እስከ መጨረሻው የሽብር ቡድኑን ለማጥፋት በቁርጠኝነት እንደሚታገልም ነው የተናገረው።
ሌላዋ የበላይ ዘለቀ ብርጌድ አባል የሆነችው ኮንስታብል ኤክራም እሸቱ ከወንድ ታጋዮች ጋር አሸባሪ ቡድኑን እየቀጣች እንደሆነ ተናግራለች።
ረዳት ኢንስፔክተር ፍቃዱ ከበደ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሆን አሸባሪውን እየቀጡት እንደሆነ ገልጸዋል። “ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር እጅና ጓንት በመሆን ጠላትን እየቀጠቀጥነው ነው” ብለዋል።
ልዩ ኃይሉ ለአማራ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ህልውናም መስዋእትነትን እየከፈለ እንደሆነ ተናግረዋል። የአማራ ልዩ ኃይል በሁሉም አውደ ውጊያዎች የጠላትን ህልም በማክሸፍ የአባቶቹን ታሪክ እየደገመ ይገኛል ነው ያሉት።
ልዩ ኃይሉ በደብረ ዘቢጥ ግንባር በርካታ የጠላትን ቡድን ከመደምሰስና ከመማረክ ባለፈ የቡድኑን የተለያዩ መሣሪያዎች መረከቡን አስረድተዋል።
“የአማራ ልዩ ኃይል ከፍተኛ ወኔን በመታጠቅ አረመኔውን ቡድን እየቀጣ ነው” ብለዋል።
አስር አለቃ ጌታቸው ጋሹ የሽብር ቡድኑን ለማጥፋት ደጀን ሕዝብ እያደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አድንቀዋል። ወደፊትም ቢሆን አሸባሪው ቡድን እስኪጠፋ ድረስ የሕዝቡ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ነው የጠየቁት። ጠላትን ለማጥፋት ልዩ ኃይሉ በአስተማማኝ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ምክትል ሳጅን አሰፋ ዓለምሰገድ የአማራ ልዩ ኃይል በሞራልና በሀገር ፍቅር በተሞላ ወኔ አሸባሪውን ቡድን እየመነጠረ ነው ብለዋል። ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሆን ከጋሳይ ጀምሮ አሸባሪ ቡድኑን እየቀጡ እንደሆነ ጠቁመዋል።
“የአማራ ልዩ ኃይል ባካሄዳቸው አውደ ውጊያዎች ሁሉ ጠላትን አይቀጡ ቅጣት እየቀጣ ነው፤ የአማራ ልዩ ኃይል ጠላት ወርሯቸው በነበሩ አካባቢዎች ለማስለቀቅ ያደረገው ተጋድሎና ጀብድ አስገራሚ ነው” ብለዋል።
ልዩ ኀይሉ ይህንን ተጋድሎና ጀብድ መፈጸሙን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ – ከኮኪት ከተማ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ