“ላሊበላ እንደ ጎል፤ ሕዝቡም እንደ ሰባ ሰገል!”

62
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ
ወልድያ፡ ታኅሣሥ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የመዳን ቀን ዛሬ ነው የተባለ ይመስላል፡፡ እልፍ ፍጡራን አልፋና ኦሜጋ የሆነውን የፈጣሪያቸውን ልደት ሊያከብሩ እልፍ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ደብረ ሮሃ ገብተዋል፡፡
የበረቱት በእግራቸው የበረከት ሥራዎችን እየሠሩ ዳግማዊ ኢየሩሳሌምን ይረግጡ ዘንድ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ በእግራቸው ያልቻሉት ደግሞ በማሕበር ኾነው እንደ ዳዊት እየዘመሩ እንደ መላዕክት እያሸበሸቡ ልደቱን በቅድስት ላል ይበላ ሊያከብሩ በጥንታዊቷ ደብረ ሮሃ ከትመዋል፡፡
ቅድስት ላሊበላ እውነተኛውን የፍቅር፣ የበረከት እና የጽድቅ ገበያ ጀምራለች፡፡ ካህናት እና መነኮሳት ብቻ አይደሉም፤ በቅድመ አባታቸው አዳም የተጠሩ ወንዶች እና በቅድመ እናታቸው ሔዋን የተጠሩ ሴቶች ኹሉ ላል ይበላ የገቡ ይመስላል፡፡ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከአዛውንት እስከ ወጣት፤ ከውጭ ሀገር እንግዶች እስከ ሀገር ውስጥ ክርስቲያኖች ልደትን በላል ይበላ ለመታደም እና ከበረከቱ ለመሳተፍ የዛጉዌ ሥርወ-መንግሥት መናገሻ እና የላስታ መዲና በነበረችው ጥንታዊቷ ደብረ ሮሃ ተሰባስበዋል፡፡
ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት በኢየሩሳሌም ሰው እና መላዕክት በአንድ ሆነው ያመሰገኑበት ጊዜ ነበር፤ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሄም ሲወለድ ነበር ይላሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፡፡ ከዚያ ዘምን ጀምረው እና የሩቅ ምስራቅ ሰዎችን ፈለግ ተከትለው ኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖች ለብዙ ዘመናት ኢየሩሳሌም ድረስ ዘልቀው የልደቱን በዓል ያከብሩ ነበር ይባላል፡፡ የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሲታነጹ ግን ያኹሉ የሲና በርሃ ጉዞ በደብረ ሮሃ ተተካ፡፡
ልደቱ ከፈጣሪው የልደት ቀን ጋር የተገጣጠመለት ቅዱስ ላል ይበላ ኢየሩሳሌም እየተሻገረ የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ያከብር ነበር ይባላል፡፡ መናኒያን ወንድሞቹ፣ መነኮሲያት እህቶቹ እና ኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ በየዓመቱ በግብጽ ምድረ በዳ የሚያደርጉት እጅግ አድካሚ፤ አልፎ አልፎ ሕይዎትን የሚነጥቅ አደገኛ ጉዞ ያበቃ ዘንድ ፈለገ፡፡ የውስጥ መሻቱን በቅንነት እና በእውነት ለሚያገለግለው ፈጣሪው “አቤት” ብሎ አሰማ፡፡
የቅዱስ ላል ይበላ የልመና እና የተማጽኖ ድምፅ ተሰምቶ ዳግማዊ ኢየሩሳሌም በሀገረ እግዚአብሔር ቅድስት ኢትዮጵያ 23 ዓመታትን የፈጁ እና ከአንድ ዓለት የተፈለፈሉ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ታነጹ፡፡ ለቅዱስ ላሊበላ በተሰጠው ቃል ኪዳን መሰረትም የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን የተሳለመ፤ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌምን እንደተሳለመ ይቆጠርለታል ያሉን በቅዱስ ላሊበላ ገዳም የዐራቱ ጉባኤያት አገልጋይ ሊቀ ጉባኤ ሃብተማሪያም ባየ ፤ኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖች በየዓመቱ የኢየሱስ ክርስቶስንም፤ የቅዱስ ላሊበላንም የልደት በዓል በጋራ ለማክበር ወደ ላሊበላ እንደሚመጡ ነግረውናል፡፡
ጥንታዊቷ ደብረ ሮሃም በቅዱሷ ሥም ሥያሜዋን ካገኘች በኋላ ከ3 መቶ 30 ዓመታት በላይ መናገሻ መሆኗ ታሪክ ሆኖ ሲቀጥል፤ የዋሻ ውስጥ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያኖቿ ደግሞ ዘላለማዊ እና ሰማያዊ ጽድቅ መዳረሻ መሰላሎች ተደርገው ተወስደዋል፡፡ ዛሬም ድረስ ከአራቱም የኢትዮጵያ አቅጣጫዎች እና ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ልደትን በላል ይበላ ለማክበር የሚመጡት ክርስቲያኖች ቁጥራቸው ከዓመት ዓመት እየጨመረ እልፍ አዕላፍ የሚባል ሆኗል፡፡
ላለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ ሰው ሰራሽ ችግሮች የቅዱሱን ልደት በላል ይበላ ማክብር ያልቻሉት ክርስቲያኖች ዛሬ ተጠቃለው ላል ይበላ የገቡ ይመስላሉ፡፡ ቅድስቲቱ ከተማ በሰዓታት ውስጥ ሰው ዘርታ ሰው ያበቀለች ትመስላለች፡፡ በቀስተ ደመና ያሸበረቁ በነጫጭ ልብሶች የደመቁ፤ ከፊታቸው ፈገግታ ከአንደበታቸው እልልታ የሚመነጭ ክርስቲያኖች ከተማዋን ሞልተዋታል፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱ እና ቅጽራቸው ተቀምጠው በጽሞና፤ ቆመው ለምስጋና በተጉ ክርስቲያኖች ተከብቧል፡፡
ላሊበላን እንደ ጎል ፤ኢትዮጵያዊያንም የክርስቶስን መወለድ ሰምተው እና በኮከብ ተመርተው ከሩቅ ምስራቅ እስከ ጎል እንደደረሱት፣ እንደሰገዱለት እና ሥጦታ እንዳስገቡለት ሰባ ሰገል ከየአቅጣጫው መጥተው ላል ይበላ ገብተዋል፡፡ ዛሬ በእርግጥም “ላሊበላን እንደ ጎል፤ ሕዝቡም እንደ ሰባ ሰገል!” ሆነው የክርስቶስን 2 ሺህ 15ኛ ዓመት የልደት በዓል እያከበሩ ነው፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!