ሊጉን በ2ኛነት የሚመራው ባሕርዳር ከተማ ዛሬ ከለገጣፎ ለገዳዲ ጋር ይጫወታል።

75

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ።
የ20ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ለገጣፎ ለገዳዲ ከባሕር ዳር ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በደረጃ ሰንጠረዡ ለገጣፎ ለገዳዲ በዘጠኝ ነጥብ 16ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጣና ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ባሕርዳር ከተማ በ39 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ለገጣፎ ለገዳዲ ካለፉት የአምስት ሊግ ጨዋታዎች አንዱን አሸንፎ በሶስት ሽንፈት አስተናግዶ በአንዱ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።
በአንጻሩ ባሕር ዳር ከተማ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች መካከለ አራቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።
ባሕር ዳር ከተማ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ነጥቡን ወደ 42 ከፍ በማድረግ የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታውን እስኪያደርግ በነጥብ እኩል ይሆናል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት የሊጉ ጨዋታ ባሕር ዳር ከተማ 2 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል።
ሌላው ጨዋታ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አርባ ምንጭ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አርባ ምንጭ ከተማ በ21 ነጥብ 12ኛ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና በ26 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
አርባ ምንጭ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን ሁለት ጊዜ ተሸንፎ ሁለቱን ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና ካለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች አንዱን አሸንፎ አራት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር እስከ ሚያዚያ 14/2015 ይቆያል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!