ሊቨርፑል ከ30 ዓመታት በኋላ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል፡፡

0
501

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 19/2012 ዓ.ም (አብመድ) የመርሲሳይዱ ሊቨርፑል ከ1989/90 (እ.አ.አ) የውድድር ዓመታት በኋላ የሊጉን ዋንጫ ወደአንፊልድ ሮድ ወስዷል፡፡

የቀድሞው ኃያል ቡድን ሊቨርፑል ከ1989/90 የውድድር ዓመታት በኋላ ከኃያልነቱ ሲንሸራተት በአርሰን ቬንገር የሚመሩት አርሰናሎችና የሰር አሌክስ ፈርጉሰን ልጆች የዋንጫ አብዮቱን አቀጣጥለው ዋንጫውን በተደጋጋሚ አነሱት፡፡ ሊቨርፑልም የበይ ተመልካች ሆኖ ቀጠለ፡፡ አብዮተኞቹም ቀስ በቀስ ከዋንጫ ፉክክር ሲወጡ ማንችሰር ሲቲና ቸልሲ ወደሊጉ አሸናፊት መጡ፡፡ በመካከልም ሌሲስተር ሲቲ ማንም ሳይጠብቀው ዋንጫ አንስቶ ዓለምን አስደመመ፡፡ በዚህ ሁሉ የታሪክ ውጣ ውረድ ዋንጫውን በአሻገር ሲመለከተው የነበረው ሊቨርፑል 30 ዓመታትን ጠብቆ ትናንት ምሽት የዋንጫ ባለቤት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

በጀመርመናዊ አቢዮተኛ የርገን ክሎፕ የሚመሩት ቀያዮቹ በአስደናቂ የአጨዋወት ስልት ተቃኝተው በ2018/19 የውድድር ዓመት ዋንጫ ለማንሳት ጫፍ ደርሰው ነበር የቀሩት፡፡ ግን ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ በዚሁ የውድድር ዓመት ከዓለም ዋንጫ በመቀጠል ትልቅ ተወዳጅነት እንዳለው የሚነገርለትን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ማንሳታቸው አጽናንቷቸዋል፡፡

የሊቨርፑል ደጋፊዎች ግን ደስታቸው ሙሉ የሚሆነው ለዓመታት የራቃቸውን የፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫን ከፍ አድርጎ መሳም ነበር፡፡ ይህ ናፍቆትም አንድ ዓመት ጠብቆ ወደ አብዮተኞቹ ተመልሷል፡፡ የሊግ ውድድሩ ሰባት ጨዋታዎች እየቀሩት ዋንጫውን ወደ ካዝናቸው ያስገቡት ቀያዮቹ በ31 የሊግ ጨዋታዎች አንድ ጨዋታ ብቻ ተሸንፈዋል፡፡ የ2019/20 (እ.አ.አ) የውድድር ዓመት ዋንጫን ማሳካታቸውን ተከትሎ ለ19ኛ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ በማንሳት 20 ጊዜ ዋንጫ ካነሳው ማንቸስተር ዩናይትድር በቅርብ ርቀት ለሌላ ታሪክ ተሰልፈዋል፡፡

ከትናንት ወዲያ በአንፊልድ ሮድ ስታዲዬም ካለደጋፊ ከክርስቲያል ፓላስ ጋር ተጫውተው 4ለ0 በማሸነፍ ቀጣይ አንድ ጨዋታ ወይም የማንችስተር ሲቲን ነጥብ መጣል ሲጠባበቁ የነበሩት ሊቨርፖሎች ትናንት ምሽት ማንቸሰተር ሲቲ በላምፓርድ ልጆች በመሸነፉ ዋንጫውን ማንሳታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ በደስታ የሰከሩ የሊቨርፑል ደጋፊዎች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጥንቃቄና ክልከላን ዘንግተው አደባባይ ወጥተው እየጨፈሩ ነው፡፡

ቸልሲ ለዋንጫ የተቃረበን ቡድን ዋንጫ ማስነሳት የተለመደ ባሕሪው ያደረገው ይመስላል፡፡ በ2013/14 (እ.አ.አ) ሊቨርፑልን አሸንፎ ዋንጫውን ለሲቲ ሲሰጥ፣ በ2015/16 የውድድር ዘመን ደግሞ ቶተንሀም ሆትስፐርስን አሸንፎ ለሌሲስተር ሲቲ ሰጥቶ ነበር፡፡ ከዓመታት በኋላ ደግሞ ማንቸስተር ሲቲን አሸንፎ ለሊቨርፑል የድል ነጋሪት ጎስሞለታል፡፡

ከትናንቱ የሲቲ ሽንፈት በኋላ የሊቨርፑል ተጫዋቾች በአንድ ላይ ሆነው ሲደሰቱ የሚያሳይ ምስል ወጥቷል፡፡ ከስካይ ስፖርት ጋር ቆይታ የነበራቸው አብዮተኛው ክሎፕ ‘‘ቃላት የለኝም፤ ይኼ የማይታመን ነው’’ ሲሉ ደስታቸውን ገልጸውታል፡፡ ሊቨርፑል በ31ኛው ሳምንት ዋንጫውን ሲያነሳ ከተከታዩ ማንችሰር ሲቲ በ23 ነጥብ ልቆ ነው፡፡ ምን አልባትም ሊቨርፑል ቀሪ ጨዋታዎችን ማሸነፍ የሚችል ከሆነ በማንችስተር ሲቲ የተያዘውን 100 ነጥብ የግሉ ማድረግ የሚችልበት ዕድል ከእጁ ላይ አለ፡፡ ዋንጫውን ሲያነሳም 86 ነጥቦችን በመሰብሰብ ነው፤ ቀሪ ሰባት ጨዋታዎችን ካሸነፈ ነጥቡን ወደ 107 ከፍ አድርጎ አዲስ ክብረ ወሰን ሊያስመዘግብ ይችላል፡፡

ምንጭ፡- ቢቢሲ
በታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here