“ለጎርጎራ ፕሮጀክት አትሌት ሻለቃ ኀይሌ ገብረሥላሴ የሚያስገነባውን ግዙፍ ሪዞርት ጨምሮ ከ120 በላይ ፕሮጀክቶች በእጃችን ይገኛሉ” የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ

0
203
“ለጎርጎራ ፕሮጀክት አትሌት ሻለቃ ኀይሌ ገብረሥላሴ የሚያስገነባውን ግዙፍ ሪዞርት ጨምሮ ከ120 በላይ ፕሮጀክቶች በእጃችን ይገኛሉ” የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ
ባሕር ዳር፡ የካቲት 13/2013 ዓ.ም (አብመድ) ጎርጎራን በገበታ ለሀገር የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም መዳረሻ አድርጎ ለማልማት ሀገር አቀፍ ፕሮጀክት ከተቀረጸ ጀምሮ በርካታ ባለሀብቶች የማልማት ጥያቄ ማቅረባቸውን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳደር አስታውቋል፡፡ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ከሁለት ወር በኋላ በይፋ ተግባራዊ መደረግ እንደሚጀምሩም ተገልጿል፡፡
ጎርጎራ የእምቅ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ናት፡፡ በአግባቡ ማልማት ከተቻለ ከዓለም አቀፍ ዘመናዊ የባሕር ዳርቻ መዝናኛዎች ጋር ተወዳዳሪ በማድረግ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ የሚቻልበት ዕድል እንዳለ አብመድ በተደጋጋሚ ዘገባዎችን ሠርቷል፡፡
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ወርቁ ኀይለማርያም እንደተናገሩት ቀደም ባሉት ጊዜያት ጎርጎራን ለማልማት የተጀማመሩ ሥራዎች ነበሩ፡፡ በተለይ በደርግ ዘመነ መንግሥት ጥሩ እንቅስቃሴ ነበር፤ በአጼ ኀይለሥላሴ ጊዜም ከሞላ ጎደል አካባቢውን የማልማት እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በ27 የኢህአዴግ ዓመታት ጎርጎራ በልማት የተረሳችና የተዳከመች መሆኗን ተናግረዋል፡፡
በዚህም የአካባቢው ማኅበረሰብ በጸጋ ላይ ተቀምጦ የሥራ ዕድል ባለመፈጠሩ ለኢኮኖሚያዊ ችግር ተጋልጧል ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይፋ ያደረጉት የገበታ ለሀገር ፕሮጀክትም ለጎርጎራ የትንሳኤ ብሥራትን ያሰማ መርሐግብር ነው ብለዋል፡፡ ጎንደርንና በዙሪያዋ ያሉ አካባቢዎችን (እስከ ባሕር ዳር) የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም እንቅስቃሴ ያነቃቃል፤ በኢኮኖሚያዊ ትሩፋቱ ጉል የሥራ እድል ፈጠራ ሚና እንደሚጫወትም አቶ ወርቁ ተናግረዋል።
ገበታ ለሀገር ጎርጎራን ለማልማት የሚፈልጉ ባለሀብቶችን ትኩረት በእጅጉ የሳበ ፕሮጀክት ነው፡፡ “ለጎርጎራ ፕሮጀክት አትሌት ሻለቃ ኀይሌ ገብረሥላሴ የሚያስገነባውን ግዙፍ ሪዞርት ጨምሮ ከ120 በላይ ፕሮጀክቶች በእጃችን ይገኛሉ” ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው፡፡ አብዛኛዎቹ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ የሚሠማሩ መሆኑንም ማወቅ ተችሏል፡፡ በተለይ አትሌት ሻለቃ ኀይሌ የሚያስገነባው ሪዞርት በሀገር አቀፍ ደረጃ ምሳሌ መሆን የሚችል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የሪዞርቱ ዲዛይን ተሠርቶ በቅርቡ እንደተመረቀም ጠቅሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ የጎርጎራ ፕሮጀክት ዲዛይን እየተሠራ ስለነበር ጥያቄ ያቀረቡ ባለሀብቶችን ፈጥኖ ወደ ሥራ ማስገባት እንዳልተቻለ አቶ ወርቁ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ የዲዛይን ሥራ መጠናቀቁን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው ዛሬ ይፋ እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡ በጎርጎራ በመንግሥት የሚሠሩ ፕሮጀክቶች ከሁለት ወር በኋላ በይፋ ተግባራዊ እንደሚደረጉም አመላክተዋል፡፡
አካባቢው በተፈጥሮ ሀብት እጅግ የበለጸገ ነው፡፡ ጎርጎራ በግብርና፣ በሆቴልና መዝናኛ እንዲሁም በሌሎች የቱሪዝም ዘርፎች ተመራጭ አካባቢ ነች፡፡ የተፈጥሯዊና የሰው ሠራሽ የቱሪዝም ሀብት መገኛ በመሆኗ በቱሪዝም ዘርፉ ብዙ መሥራት እንደሚቻልም አብራርተዋል፡፡
አካባቢው የመስኖ ልማት ያለበት በመሆኑም በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በአበባ ልማትና በሌላም የግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ማልማት ይቻላል፡፡ ጎርጎራ ለአምራች ኢንዱስትሪም ተመራጭ መዳረሻ ነች፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብም ከፍተኛ የመልማት ፍላጎት አለው፡፡
የዞኑ አስተዳደርም አካባቢው በተገቢው መንገድ እንዲለማ ከቢሮክራሲ የጸዳ አገልግሎት ለመስጠት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ባለሀብቶች የሚጠበቅባቸውን እስካሟሉ ድረስ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚደረግም አመላክተዋል፡፡ ባለሀብቶች ጎርጎራን በማልማት ለአካባቢው ብሎም ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here