ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዘንድሮ ለሚሰጠው የዩኒቨርሲቲዎች የመውጫ ፈተና በቂ ዝግጅት እያደረኩ ነው አለ የትምህርት ሚኒስቴር፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አገልግሎት ዘርፍ ዳይሬክተር ኢዮብ አየነው (ዶ.ር)፥ በዚህ ዓመት ለሚሰጠው የዩኒቨርሲቲዎች የመውጫ ፈተና ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት ከ230 ሺህ በላይ ተማሪዎች ፈተናውን ለመውሰድ የተመዘገቡ ሲሆን፥ ቁጥሩ ከዚህ በላይ ከፍ እንደሚል ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ሚኒስቴሩ የመውጫ ፈተና አተገባበር መመሪያ አዘጋጅቶ ለትምህርት ተቋማት ማሰራጨቱ ተጠቅሷል።
ተማሪዎች ከወሰዷቸው የተለያዩ የትምህርት አይነቶች ውስጥ በአማካኝ ከ10 እስከ 17 የሚሆኑት ተለይተው በመውጫ ፈተናው እንደሚፈተኑ አስረድተዋል።
በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በበይነ መረብ ለሚሰጠው የመውጫ ፈተናም ከ34 ሺህ በላይ ኮምፒውተሮች መዘጋጀታቸውንም ነው የተናገሩት።
የመብራት መቆራረጥ ችግር ቢያጋጥም እንኳን ጀኔሬተር የተዘጋጀ ሲሆን የኢንተርኔት እና ሌሎች ችግሮች እንዳያጋጥሙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ ይገኛልም ነው ያሉት።
ከመጋቢት 15 ቀን ጀምሮ በ210 የትምህርት ፕሮግራሞች እየተዘጋጀ የሚገኘው የመውጫ ፈተናም ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ወደ መጠናቀቁ መቃረቡንም አንስተዋል።
ለተማሪዎችም የትምህርት ተቋማት የሥነ ልቦና እና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን እየሰጡ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።
በመመሪያው ላይ ትምህርት ሚኒስቴር በዓመት ሁለት ጊዜ የመውጫ ፈተና የሚሰጥ ሲሆን፥ የተቀመጠውን የመቁረጫ ነጥብ ማምጣት ያልቻሉ ተፈታኝ ተማሪዎችም ዝግጅት ካደረጉ በስድስት ወር ውስጥ ተመዝግበው መፈተን ይችላሉ ፡፡
ተማሪዎች መታወቂያ (አይ ዲ ካርድ) ከተሰጣቸው በኋላ በሚፈልጉት ቦታ ተመዝግበው መፈተን የሚችሉ ሲሆን ማንኛውም ተማሪ እየከፈለ ያለ ጊዜ ገደብ ይፈተናል ነው ያለው ሚኒስቴሩ ፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!