“ለውጥ የሚመጣው ለውጥን በመፈለግ ብቻ ሳይኾን ጠብታ ተግባርም ሲጨመርበት ነው” ዶክተር ማተብ ታፈረ

0
86
ባሕር ዳር: ሕዳር 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባዔ የክልሉን ትምህርት ቢሮ የ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል፡፡ የተቋሙን የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ማተብ ታፈረ (ዶ.ር) ባልታሰቡ ክፍተቶች የተፈተነውን የሩብ ዓመት አፈጻጸም ችግሮችን ተቋቁሞ ለመሻገር በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል ብለዋል፡፡
የአንዲት ሀገር መጻዒ እጣ ፋንታ የሚወሰነው ለትምህርት በሚሰጠው ትኩረት እና በሚመዘገበው ውጤት ላይ ነው ያሉት ዶክተር ማተብ አሁን ባለው የትምህርት ቤቶች ቁመና እና ግብዓት የተሻለ መማር ማስተማር መፈጸም ፈታኝ ኾኗል ብለዋል፡፡
“ለውጥ የሚመጣው ለውጥን በመፈለግ ብቻ ሳይኾን ጠብታ ተግባርም ሲጨመርበት ነው” ያሉት ዶክተር ማተብ ለክልሉ ምክር ቤት አባላት፣ ለክልሉ ምሁራን፣ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ለትምህርት ባለድርሻ አካላት ትኩረት ቢሰጥ ያሏቸውን ነጥቦች አንስተዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት መዋቅራዊ ድጋፍ እና ትኩረት ሊያደርግ ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር ማተብ የትምህርት ቁሳቁስን ማሟላት ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ በመኾኑ የበጀት ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡ በሀገር ውስጥ የማይገኙ የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላትም ቢሮው የውጭ ምንዛሬ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ተቋማት መካከል መሆን ይገበዋል ነው ያሉት፡፡ የክልል ቢሮ ኅላፊዎች እና ምክትል ኅላፊዎች ፈንድ አፈላልገው እና ማኅበረሰቡን አስተባብረው በየትውልድ ቀያቸው አንድ አንድ ትምህርት ቤቶችን ማሠራት እና አርዓያ እንዲኾኑም ዶክተር ማተብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሌላ በኩል ትምህርት በርካታ ባለድርሻዎችን ያቀፈ ተቋም ነው ያሉት ቢሮ ኅላፊው የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባዔ እና በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉባዔ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ ትምህርት በየጊዜው የሚሻሻል፣ ቴክኖሎጂን የሚፈልግ እና ግብዓት የሚሻ በመኾኑ የምሁራን መማክርት ጉባዔ የጎላ አበርክቶ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በአካባቢያቸው ሞዴል የሚኾኑ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት አስተማሪ እና አርዓያ ሊኾኑ ይገባል ነው ያሉት፡፡
የክልሉ ምክር ቤት አባላት ከተለመደው ድጋፋቸው ወጥተው የተማሪዎችን ሥነ ምግባር ቀረጻ እና ግብዓት በማሟላት ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ተብሏል፡፡ የምክር ቤት አባላት ትምህርትን በመደገፍ ጉልህ ሚና አላቸው ያሉት ዶክተር ማተብ ከተለመደው ወጥቶ የምክር ቤት አባላት በተመረጡበት አካባቢዎች የተማሪዎችን ሥነ ምግባር በማሻሻል እና ተከታታይ ውይይቶችን በማድረግ ሊያግዙ ይገባል ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሕዝቡን አስተባብረው ትምህርት ቤቶችን ቢገነቡ እንደ አስፈላጊነቱ ስማቸውን በትምህርት ቤቱ ሕንጻዎች እንደሚሰይሙም ቃል ገብተዋል፡፡
በመጨረሻም የተማሪዎች ምገባ ከትምህርት ተሳትፎ በዘለለ ለትምህርት ጥራት መሻሻልም ያግዛል ያሉት ዶክተር ማተብ ጉዳዩ ከመንግሥት በጀት በዘለለ የትምህርት ባለድርሻ አካላትን ንቁ ተሳትፎም እንደሚጠይቅ አስረድተዋል፡፡ በምግብ እጥረት ምክንያት በርካታ ተማሪዎች ትምህርት ያቋርጣሉ ያሉት ዶክተር ማተብ የተቀናጀ ድጋፍ ያስፈልገዋልም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!