“ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያጋልጠው እና በሕገ ወጥ ደላሎች አሳለጭነት የሚከናወነውን ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በትኩረትና በጥምረት ልንከላከለው ይገባል“ አቶ ዣንጥራር አባይ

61

አዲስ አበባ: ግንቦት 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ፍትሕ ቢሮ ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፍትሕ ቢሮ ጋር በመኾን በሰው የመነገድ ድርጊት እና በሕገ-ወጥ መንገድ ሰዎችን ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር አጠቃላይ አደረጃጀት እና አሠራርን በተመለከተ የልምድ ልውውጥ መድረክ አካሂደዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ዣንጥራር አባይ በመድረኩ የሥራ መመሪያ ሲሰጡ እንደተናገሩት በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ምክንያት ለሚፈጸሙ ወንጀሎች በዋናነት ሕገ ወጥ ደላሎች በመሆናቸው እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመከላከል በጋራ መስራት ያስፈልጋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ እና የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚከላከል ደንብ ማጽደቃቸውንም ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ተክሌ በዛብህ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጸምበት በመኾኑ በትኩረት እና በጥምረት ልንከላከለው ይገባል ብለዋል። ድህነት፣ ሥራ አጥነት፣ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ፣ የጓደኛ ግፊት እና መሠል ምክንያቶች ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አባባሽ ኹኔታዎች እንደኾኑም ገልጸዋል።

የሕገ ወጥ የሰዎችን ዝውውር የሚያከናውኑ ሕገ ወጥ ደላሎችን ማጋለጥ እና ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በማድረግ ሂደት ኀብረተሰቡ ከጸጥታ ተቋማት ጋር በጥምረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ፍትሕ ቢሮ ችግሩን ለመከላከል የሚያስችል መመሪያና ደንብ ማጽደቁን እና ወደፊት አበረታች ውጤት እንደሚያመጣ እምነታቸውን ገልጸዋል።

አዲስ አበባ ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝዉዉር ምቹ ከተማ ነች ያሉት የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ገረመው ገብረ ጻዲቅ እንዲህ ዓይነት ወንጀሎች ውስብስብ በመኾናቸው በትብብር መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከለል ያጸደቀው ደንብና መመሪያ ለአማራ ክልል ጥሩ ተሞክሮ የሚኾን ነውም ብለዋል።

ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!