“ለኢትዮጵያ ክብር የዘመቱትን መሪ ተከተላቸው፣ ጠላቶችህንም አጥፋቸው”

0
185
ሕዳር 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ምን አይነት ሀገር ነው ያለችን ? ምን አይነትስ ሕዝብ ነን? ሲገፉን የምንጠነክር፣ ሊነጣጥሉን ሲሞክሩ የምናብር፣ ሊጥሉን ሲሞክሩ የምንጥል? ሥሪታችን ምንድን ነው? ኃይላችንስ ምኑ ጋር ነው? አጀብ ነው እኮ ከዘመን ዘመን የሚመጣ ጠላት በበዛበት ዓለም ውስጥ ሁልጊዜ ማሸነፍ ብቻ። ከማሸነፍ ውጭ ሌላ የማታውቅ ድንቅ ምድር። በአሸናፊነት የፀናች ኃያል ሀገር። ማነው ከእርሷ ጋር የሚተካከል? ማነው እርሷን የሚያሸንፍ? የክብሯን ወሰን የሚያልፍ? ከሁሉም የቀደመች፣ በክንዷ የታፈረች፣ በልጆቿ ደምና አጥንት፣ ሕይወትና ፀሎት የተጠበቀች።
ኢትዮጵያን አትንኳት ታቃጥላለች፣ አትግፏት ትጥላለች፣ አትነሱባት ተሰነስታ ታጠፋለች፣ እንዳልነበር ታደርጋለች፣ ሊያዋርዷት ካሰቡ ታዋርዳለች፣ ሊያስደፏት ከቋመጡ አስቀድማ አንገት ታስደፋለች። ለነብሱ የማይሳሳ ጦረኛ ወታደር ያለባት፣ አባቶች ዓለምን ረስተው፣ ምቾትን ንቀው የሚፀልዩባት፣ ምልጃ የሚቀበሉባት፣ ቃል ኪዳን የሚያሰጧት፣ ፈጣሪ የመረጣት፣ አስቀድሞ ያከበራት፣ በአሸናፊነት ያኖራት፣ በፍርድ ቀን ለምስክርነት ያስቀመጣት፣ የመረጣት፣ አራሽና ተኳሽ፣ ሶላት አድራሽና ቀዳሽ፣ አስቀዳሽ ያሉባት ውብ ሀገር። ክፉ መካሪዎች ሁሉ ተነስተውባታል። እናጥፋት፣ እናፍርሳት፣ እናሳንሳት ሲሉ መክረውባታል፣ ጦር አዝምተውባታል። እርሷ ግን ክፉ መካሪዎችን አጠፋች፣ እናፍርሳት ያሉትን እስከ ሐሳባቸው ድረስ አፈረሰች፣ ጦር ያዘመቱባትን በጦር ቀጣች፣ በክንዷ አስገበረች። እስከዛሬም በታላቅነት ኖረች።
በኢትዮጵያ ጠላት በተነሳ ቁጥር መሪዎቿ አዋጅ አስነግረው፣ ቃል ኪዳን አስረው ዘመቻ ይጠራሉ፣ ፈረሶቻቸውን ጭነው፣ ስንቃቸውን ሰንቀው፣ መኳንንቱንና መሳፍንቱን፣ ሠራዊቱንና አጋፋሪውን፣ የእልፍኝ አስከልካዩንና ዓለም አጫዋቹን ይዘው፣ ተቆጥተው ይነሳሉ፣ ሕዝባቸውም ተቆጥቶ ይከተላቸዋል። ሠንደቁን አስቀድመው፣ በጋራ መክረው፣ በጋራ ወግተው፣ በጋራ አሸንፈው ይመለሳሉ። ኢትዮጵያውያን መሪዎች ከማዘዝ ያለፈ ተግባር አላቸው፣ ዘምተው ያሳያሉ፣ ዘምተው ይዋጋሉ፣ ዘምተው ያዋጋሉ፣ ከዙፋን ወርደው በምሽግ ያድራሉ፣ በንግሥና በትራቸው ፋንታ ጎራዴና ጦር ይጨብጣሉ፣ ጋሻውን ያነሳሉ፣ በጋሻው መክተው፣ በጦሩ ወግተው፣ በጎራዴው ሸልተው ጠላቶቻቸውን ይመልሳሉ። ይደመስሳሉ። ሀገራቸውን በደም ዋጋ ያፀናሉ።
ነገሥታት ኢትዮጵያ ተነካች ሲባሉ ንግሥናቸውን ይረሳሉ። ምቾታቸውን ይተዋሉ። በቤተ መንግሥት በዙፋን ተቀምጠው፣ ይህን አድርጉ ይህን አታድርጉ ማለት ይተዋሉ። ይሄን ላደርግ ነውና ተከተሉኝ ብለው ይነሳሉ። የገቡትን ቃል ኪዳን ይፈፅማሉ። ኢትዮጵያዊያንም ነገሥታቶቻቸውን ይከተሏቸዋል፣ አለን ይሏቸዋል። ትጥቅና ስንቅ አዘጋጅተው ቆርጠው ይነሳሉ። ከነገሥታቶቻቸው ጋር አሸንፈው ይመለሳሉ። በየዘመናቱ የተነሱት ነገሥታት ዘምተው አዝምተዋል ፣ ተዋግተው አዋግተዋል፣ ግዳይ ጥለው አሳይተዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ስሙ ከፍ ብሎ የሚነሳውን የዓድዋን ታሪክ ብናነሳ አባ ዳኘው ምኒልክ ፈረሳቸውን ጭነው ዘምተዋል፣ አዝምተዋል፣ ተዋግተው አዋግተዋል። እንደ ሠራዊታቸው በዱር በገደል አድረዋል፣ ተጠምተዋል፣ ተርበዋል፣ ባለቤታቸው ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ እምዬን ሸኝተው፣ እኔ በቤተመንግሥት ልሰንብት፣ እናንተ ተዋጉ ብለው አልቀሩም። ከሀገር በላይ ማንም የለምና ፈረስ ጭነው፣ ዘማች አስከትለው፣ የጦርነት ስልት ነድፈው ዘምተዋል፣ አዝምተዋል ፣ አሸንፈው ተመልሰዋል። ምኒልክ በመሩት ጦርነት ዓድዋ ተገኘ። ነጭ ደነገጠ፣ ጥቁር ነፃ ወጣ፣ በዓለም ላይ ፍትሕ መጣ። ፀሐይ በምሥራቅ ወጣ። ዓፄ ኃይለ ሥላሴ አባ ጠቅልን ጭነው ማይጨው ድረስ ዘምተዋል። ተዋግተው አዋግተዋል።
ከዚያ በፊት የነበሩት ነገሥታት ሁሉ እነ አምደ ፅዮን፣ እነ ልብነ ድንግል፣ እነ ገላውዲዮስ፣ እነ ሚናስ እነ ሠርፀ ድንግልና ሌሎችም ከዙፋናቸው ወርደው ዘምተዋል፣ አዝምተዋል፣ ተዋግተው አዋግተዋል። በቀደሙት ዘመናት የነበሩት አያሌ ነገሥታት ይህን አድርገዋል። በኢትዮጵያ ላይ የተነሳውን ቀጥተዋል። ሀገራቸውን አፅንተዋል። ቴዎድሮስ አያሌ ጦሮችን መርቷል። በድንቅ ጦረኝነቱ ጠላትን ቀጥቷል። የዘመነ መሳፍንት ከፋፋዮችን መልክ አስይዟል። አንዲት ሀገር አስፈሪ ዙፋን መስርቷል። ይህን ሁሉ አድርጎ አልበቃ ሲለው ራሱን ለኢትዮጵያ ፍቅርና ክብር ሲል ሰጥቷል። ሀገርን ከምንም በላይ እንደሆነች አሳይቷል። የኢትዮጵያ ነገሥታት የሚታወቁበት አንደኛው ይሄ ነው።
ንጉሥ ሆነው ሳለ እንደ እግረኛ ጦረኛ ይዋጋሉ፣ መቀመጫቸው ዙፋን ሆኖ ሳለ በጦር ግንባር ያደራሉ፣ ልብሳቸው በወርቅ የተለበጠ፣ በአልማዝ ያሸበረቀ ሆኖ ሳለ ያን ረስተው የጦር ሜዳ ልብስ ያጠልቃሉ፣ ጦር ያነሳሉ። ከሠራዊታቸው ጋር እኩል ይዋጋሉ። ድልም ያገኛሉ። በዚህ ጀግንነታቸው፣ በዚህ አትንኩኝ ባይነታቸው ትውልድ ሁሉ የሚኮራባት፣ የተበደለ ሁሉ ተስፋ የሚያደርጋት፣ ጠላት ሁሉ የሚፈራት፣ ጥቁሮች ሁሉ ምልክት የሚያደርጓት ሀገር አቆይተዋል።
“ሰማን ክብሯ ባለም ገኖ ሲነገርላት፣
ጥንትም አንበሳ ነው የእርሷ ምልክት” እንደተባለ የእርሷ ምልክት አሸናፊው ነው፣ የጀግኖች ጀግና አንበሳው ነው፣ ስሟ በዓለም ገኖ የሰማነው የአሸናፊዎች ሀገር ስለሆነችና በአሸናፊነት ስለ ደመቀች ነው። ዘመን ዘመንን ተካና የራስን ታሪክ የመሥራት ዘመን መጣ። እነሆ ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ በውስጥ ባንዳዎች፣ ከሃዲዎችና በውጭ አዛዦች ጥምረት በተከፈተባት ጦርነት ውጊያ ላይ ናት። ውጊያው ዘርፈ ብዙ ነው። አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ኃይል ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች ጋር በመቀናጀት ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየተፍጨረጨረ ነው። ኢትዮጵያውያንም በጋራ የመጡባቸውን ጠላቶች በጋራ ለማጥፋት ተቆጥተው ተነስተዋል። ቆርጠው ወጥተዋል።
የዚህ ዘመን የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን መሪ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እንደ ቀደሙት ነገሥታት ሁሉ ወደ ጦር ሜዳው እዘምታለሁ። እመራለሁ፣ አዋጋለሁ ብለዋል። ቃል አስረዋል። በኢትዮጵያ ደማቅ ታሪክ ላይ የደመቀ ታሪክና የደመቀ ስም እንዲኖረው የሚሻ ኢትዮጵያዊ ሁሉም ይከተለኝ ብለዋል። መሪህ ቀድመዋል። በውስጥህ ምንም ይኑር ሀገር ግን ሀገር ናት። በምንም ነገር የማታወዳድራት። በምንም ነገር የማትቀይራት። ለአንድ ዓላማ፣ ለአንዲት ሀገር፣ ለነፃነት፣ ሉዓላዊነት ተነስ ተብለሃል ተነስ፡፡ ተከተለኝ ተብለሃልና ተከተል። ስትከተል አትጠራጠር፣ ከፊትህ ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ ሠንደቅ ነውና ያለው። ከቤተ መንግሥት ወጥተው በምሽግ ማደርን መርጠዋል። እንደ እግረኛ ሠራዊት ኮቸሮና የኮዳ ውኃ ለመጠጣት፣ ለኢትዮጵያ ሁሉንም ለመስጠት ተከተሉኝ ብለው ቀድመዋል።
መሪህን ተከተላቸው። በኢትዮጵያ ምድር የተፈጠሩ ብዙ ጠላቶችና በመላው ዓለም ከሚኖሩ እልፍ ጠላቶች ጋር እንደገጠምክ አትዘንጋ። ውጊያው እንደ ዓድዋው ከውጭ ጠላቶች ጋር ብቻ አይደለም። በእርግጥ በዚያ ዘመንም የውስጥ ባንዳዎች ነበሩ። ገሚሶቹ አካሄዱን አይተው በመካከል ንጉሣቸውና ሀገራቸውን ደግፈዋል። የቀሩትም ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር አብረው ተቀጥተዋል። ተሸንፈዋል። የአሁኑ ባንዳና ከሃዲ ከዚያ ዘመን ይበልጣል። ከጦርነቱ ውሸቱን እያስቀደመ የሚመጣ ሀገር ሻጭ ነውና፡፡
ተጠንቀቅ፣ ፅና፣ ባሕሪውን ልመድ። መሪህ ተነስተዋል። ጠላትን አጥፍተው ኢትዮጵያን ለማፅናት ቆርጠው ወደ ግንባር ገስግሰዋል። እንደ ቀደሙት ኢትዮጵያውያን ተከተላቸው፣ ሥንቅና ትጥቅህን ይዘህ አለሁ በላቸው። በሀገርህ ላይ ደማቅ ታሪክ ፃፍ፣ የመከራውን ዘመን በጥበብ እለፍ፣ ማዕበሉን ተሻገር፣ ሀገርህን አስከብር።
የአንድነት የድል ዋጋ እየተባለ የሚጠራው ዓድዋ በመሪውና በተመሪው የነበረው አንድነት የብስ አቋርጦ፣ ባሕር ሰንጥቆ የመጣውን ጠላት በእኩለ ቀን ውጊያ ነው ድምጥማጡን ያጠፋው። አንተም ከመሪህ ጋር አብረህ፣ ልዩነትን ለጊዜው ወደ ጎን ተትህ ከተነሳህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ድምጥማጡን አጥፍተህ፣ ሀገርህን ሰላም ታደርጋለህ። ተነስ ከተቀመጥክበት ተከተላቸው፣ አለሁ ብለህ አጅባቸው። ያን ጊዜ ጠላቶችህ ይደነግጣሉ። መውጫ መግቢያ ያጣሉ። እርር ኩርትም ይላሉ። ዛሬ ሀገርህ ጠርታሃለች፣ እምዬ ና ብላለች። እርሷ ስትጠራህ ከቀረህ፣ ነገ ላይ የመናገር አቅሙም የለህ። ደጋፊም ነቃፊም ለመሆን ትቸገራለህ። ለምን? ካልክ የሚጠበቅብህን አላደረክምና። ገስግስ ድልህ ይፍጠን።
መሪህ ምሽግ ገብተው፣ ነፍጥ አንስተው አንተ ከቤትህ ካደረክ የሀገር ትርጉሙ፣ የኢትዮጵያዊነት ውሉ አልገባህም ማለት ነው። እየመሩህ ነውና ተከተላቸው፣ በውጭና በውስጥ የመጣውን ጠላት ጥለህ አሳያቸው። ተነስ ዓለማት ይግረማቸው፣ በአድራጎትህ ይድነቃቸው። በዚያች ድንቅ ምድር ዛሬም እንደ ትናንቱ አንድነት አልጠፋም። ጀግንነት አልጠወለገም ይበሉ። ይገረሙ። ኢትዮጵያን ብሎ፣ በኢትዮጵያዊነት አምኖ፣ በሠንደቁ ምሎ የተነሳው ሁሉ ተሸንፎ አያውቅም። ዛሬም አይሸነፍም።
አዎን መሪህ ዘምተዋል። አንተም ዝመት፣ ጠላትህን እስከወዳኛው አሰናብት። በድልህ ዓለማት ይገረማሉ። በኢትዮጵያ ላይ የዘረጉትን የክፋት እጃቸውን ይሰበስባሉ። ወዮልን ወዮታ አለብን ይላሉ። አሁን ተነስ ተከተላቸው። ለጠላቶችህ በደምህና በአጥንትህ ደማቅ ታሪክ ጽፈህ አሳያቸው። እምብኝ በቃ በላቸውና ይግረማቸው። ድል ያለው ከኢትዮጵያ ጋር ነው። ብቻ ተነስ።
በታርቆ ክንዴ
ተነሳ!!
መሪህን ተከተል!!
ሀገርህን አድን!!
ነፃነትህን አትስጥ !!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ