ለአፍሪካ ነፃነት-የኢትዮጵያ ተምሳሌት
ባሕር ዳር፡ የካቲት 16/2013 ዓ.ም (አብመድ) በዓለማችንን የፖለቲካ ኀይል አሰላለፍ የታላላቆቹ ትኩረት ከዚህ አካባቢ ለአፍታ እንኳን አይጠፋም፡፡ ቦታውን የሚፈልጉት የጥንት አውሮፓዊያን በቅኝ ግዛት አያት ቅድመ አያቶቻችንን ከቀያቸው ፈቀቅ ለማድረግ ያላደረጉት ጥረት አልነበረም፡፡ በተለይም የአፍሪካ ቀንድ እስከ ቀይ ባህር ዳርቻ በሚዘረጋው የቀጣናው ጂኦ ፖለቲካል ንክኪ በአራቱም አቅጣጫ የዓለምን ትኩረት ለመሳብ ከጥንት እስከ ዛሬ የተለየ ያደርገዋል፡፡
በበርካቶች ዘንድ የአፍሪካ ቀንድ ሲነሳ ቀድማ የምትታወሳቸው ደግሞ ኢትዮጵያ ናት፡፡ በማንም ያልተደፈረ የዕድሜ ዘመን ነፃነት፣ ውብና የቀሪውን ንፍቀ ክበብ ቀልብ የሚስብ ባህል፣ በመቻቻልና በመከበባር ላይ የተመሰረተ የእምነት ልዩነት፣ በልዩነት ውስጥ አንድነት፣ ቀደምት ቋንቋ እና እሴት ተንሰላስለው በበርካቶች አዕምሮ በቀላሉ እንዳትጠፋ የታተመች ስዕል አድርገዋታል-ኢትዮጵያን፡፡
ኢትዮጵያ የደም ገንቦ፤ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ የውበት ዳርቻ ነው፡፡ መልክዓ ምድሯ ድሪ፣ ልምላሜዋ አልቦ፣ ነፃነቷ ድንግልና እንዲሁም የልጆቿ አጥንት እና ደም እንሶስላ ሆኖ እስከ አሁኑ ትውልድ ድረስ ያደመቃት የውበት ሰገነት ናት፡፡
በየዓመቱ በዓለም የታሪክ ድርሳን ወርሃ የካቲት ሲወሳ የጥቁሮች የነፃነት ተጋድሎ እና ድል ሚዛን ደፍቶ ይታያል፡፡ የዚያ ዘመን ጥቁሮች የነፃነት ድል ጉልላት ደግሞ አድዋ ነው፡፡ አድዋ የቅኝ ገዥዎች አከርካሪ የተሰበረበት እና መላው የዓለም ጥቁር ክብር የተቀዳጀበት ድል ነው፡፡
በጦርነት እና በኀይል አፍሪካን መያዝ ጀምበር እየጠለቀችባቸው መሆኑን የተረዱት ወራሪዎቹ አካባቢውን ላለመልቀቅ እና አፍሪካውያንን ነጻ ላለማድረግ ሌላ የዲፕሎማሲያዊ አውድ ፈጠሩ፡፡
‹‹ራሳችሁን ለመቻል የሚያስችል የታሪክ ድርሳን የተከተበበት ቋንቋ እንኳን አልነበራችሁም›› በማለት አፍሪካዊያን በቅኝ ግዛት መቆየታቸው ፍትሐዊ ነው ለማለት ዳዳቸው፡፡ ነገር ግን ከአድዋ ድል በኋላም ቅኝ ገዥዎችን በዲፕሎማሲያዊ መድረክ ብርክ ያስያዘ ሌላ ታሪካዊ ድል ስለመኖሩ ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን?
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል የታሪክ መምህር እና በኢትዮጵያ የመካከለኛው ዘመን ታሪክ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ እና ተመራማሪ የሆኑት ዘመነወርቅ ዮሐንስ የሚሉት አላቸው፡፡
የታሪክ ተመራማሪው መምህር ዘመነወርቅ ዮሐንስ እንዲህ ይላሉ እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር በ1960ዎቹ አካባቢ ወራሪዎቹ የፋሽዝም እና ናዚዝም አቀንቃኞች በቅኝ ግዛት አፍሪካ ውስጥ የመቆየታቸው ዕድል እየጠበበ መጥቷል፡፡ ቀሪ ዘመናቸውን ለማመቻቸት እና የወረራ ጊዜያቸውን ለማራዘም የሚያስችል መድረክ ግን በአፍሪካ እና በመላው አውሮፓ ሀገራት ፈጥረው ውይይት ጀምረው ነበር፡፡
በእነዚህ መድረኮች ሁሉ ተደጋግሞ የሚነሳ አንድ ጥያቄ አለ እርሱም ‹‹ለመሆኑ እናንተ ወንዝ ተሻግራችሁ፤ ድንበር አቋርጣችሁ መጥታችሁ አህጉራችን የወረራችሁበት ምክንያት ምንድን ነው?›› የሚል፡፡ በተደጋጋሚ ለሚነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጡ የተገደዱት አውሮፓዊያን ቅኝ ገዥዎች ሲመልሱም በመጀመሪያ ደረጃ የመጣነው መምጣት ስላለብን ነው፡፡ ለምን ቢባል በዚህ ክፍለ ዓለም ውስጥ የሚኖረው ጥቁር ህዝብ በዓለም ስልጣኔ ጉዞ ውስጥ የራሱ የሆነ አሻራ የለውም፡፡ አፍሪካ እና አፍሪካዊያን በዓለም የስልጣኔ እርሾ አልባ ናችሁ፡፡ ለዚህ ማሳያው ደግሞ የራሳችሁን የቀደመ ታሪክ ለትውልድ የምታስተላልፉበት የራሳችሁ ቋንቋ እንኳን የላችሁም፡፡
ዛሬ እናንተ ጥቁር አፍሪካዊያን የምትጠቀሙበት የፈረንሳይ፣ የፖርቹጋል፣ የጣሊያን እና የእንግሊዝ ቋንቋዎች ከሌላው ዓለም ህዝብ ጋር ስላግባቧችሁ የእናንተ አድርጋችሁ ወስዳችሁ ከሆነ ተሳስታችኋል፡፡
አፍሪካ ቋንቋ እንኳን የሌላት አህጉር ናት የሚል ነበር የወረራ እና የቅኝ ግዛት አመክንዮአቸው፡፡ በመላው አፍሪካ ንቅናቄ (ፓን-አፍሪካኒዝም) ጥላ ስር ሆነው ለነፃነታቸው የሚታገሉት ጥቁር አፍሪካዊያን ለምላሽ ተዘጋጁ፡፡ ይህንን የፋሺዝም እና ናዚዝም አቀንቃኞች አመክንዮ በማፍረስ፤ በደም እና በአጥንት ከተከበረው ነፃነት ባልተናነሰ በዲፕሎማሲው መስክ ገድል በመፈፅም ለአፍሪካ ሀገራት ነፃነት ኢትዮጵያ በድጋሜ መውጫ ቀዳዳ ሆና ተገኘች ይላሉ መምህር ዘመነወርቅ፡፡
መምህር ዘመነወርቅ የያኔዎቹ የአፍሪካ አህጉር የነፃነት ታጋዮች ወራሪዎቻቸውን እንዲህ አሏቸው “አፍሪካ የራሷ የሆነ ቋንቋ አላት፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ ከእስልምና ሃይማኖት መምጣት ቀጥሎ በእጅ የተፃፉ ኪታቦቻችን ታገኛላችሁ፡፡ ከአፄ አምደ ፅዮን ዜና መዋዕል ጀምሮ የተከተቡ ድርሳናት ቀደምት ታሪካችንን ይነግሯችኋል፡፡ ብራና ፍቀው ቀለም በጥብጠው ታሪካችንን የከተቡት አያት ቅድመ አያቶቻችን ምን ያክል ጠቢባን እንደነበሩ ጥበብን ታያላችሁ፡፡ የድንጋይ ላይ ጽሑፎቻችን የእናንተ አባቶች ስለጽሑፍ ሳይገባቸው የእኛዎቹ ገብቷቸው እንደነበር ይገባችኋል” የሚል ነበር፡፡
ለማመን የተቸገሩት ቅኝ ግዥዎች ደጋግመው መጥተው ኢትዮጵያን የመፈተሻቸው ሚስጥርም ቀደምትነታችን ነበር፡፡ ትናንት ኢትዮጵያ በየትኛውም አውድ አፍሪካን ቀደምት ብላ አስጠርታለች የሚሉት መምህር ዘመነወርቅ ዮሐንስ ትውልዱ የአያት ቅድመ አያቶቹን ሀገር ሊያስቀጥል ከተፈለገ የትናንቱን ታሪክ ሊማርበት ይገባል ባይ ናቸው፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ