ለአጣዬና አካባቢው እንዲሁም ለኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ተፈናቃዮች የአይነት እና የገንዘብ ድጋፍ ተደረገ።

0
70

ለአጣዬና አካባቢው እንዲሁም ለኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ተፈናቃዮች የአይነት እና የገንዘብ ድጋፍ ተደረገ።

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 24/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ለአጣዬና አካባቢው እንዲሁም ለኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ተፈናቃዮች የ50 ሚሊዮን የአይነት እና የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፋንታ ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ አልማ ከልማቱ ጎን ለጎን በተለያዩ ጊዜያት በሚከሰቱ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች የጉዳቱ ተጠቂ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሕዝቡን በማስተባበር የዕለት ደራሽ ድጋፍ በማድረግ በዘላቂነት ማቋቋም ላይ ያተኮረ እቅድ አዘጋጅቶ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።

ለአጣዬ አካባቢዋና ለኦሮሞ ብሔረሰብ ተፈናቃዮች በሚደረገው የእለትደራሽ ድጋፍ በምግብ እጥረት ሕይወቱን ያጣ ሰው የለም፤ ተፈናቃዮቹን በዘላቂነት ከማቋቋም አንጻር መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት እቅድ ታቅዶ ትርጉም ያለው ሥራ እተሠራ መሆኑና በግንባታውም ከ450 በላይ የአካባቢው ወጣቶች የሥራ እድል መፈጠሩን አቶ መላኩ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ለሁለቱም ዞን ተፈናቃዮች ለሁለት ጊዜ ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰው በዲያስፖራው ኮሚቴ በኩልም ከ5 መቶ ሺህ ዶላር በላይ ቃል ተገብቶ ከዚህ ውስጥ 2 መቶ ሺህ ዶላር ወደ ባንክ አካውንት ገቢ ተደርጓል ብለዋል።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዘላለም ልጅዓለም በሁለቱ ዞኖች በተከሰተው የጸጥታ ችግር ለተፈናቀሉ ዜጎች ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመቀናጀት ከ70 ሺህ በላይ ኩንታል እህል መሰራጨቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ተፈናቃዮቹ ተረጋግተው ወደ ቀድሞ ቀያቸው እንዲመለሱ በርካታ ሥራዎች በመሰራታቸውና አንጻራዊ ሰላም በመፈጠሩ የሁለቱም ዞን ነዋሪዎች ወደ መደበኛ የእርሻ ሥራቸው መግባታቸው ትልቅ አቅም ነውም ብለዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረጻድቅ ለዞናችንና ለኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ተፈናቃዮች አልማን ጨምሮ በተለያዩ አካላት አስተባባሪነት ችግሩ ከተከሰተ ጀምሮ ድጋፍ ሲያደርጉ ለቆዩ አካላት ምሥጋና አቅርበዋል። ተፈናቃዮቹን በዘላቂነት ለማቋቋም ድጋፋቸው ተጠናክሮ እንድቀጥል ጠይቀዋል።

በገጠረ የ78 ቤቶች ግንባታ ቢጀመርም ሌሎቹን ፈጥኖ ለማጠናቀቅ በክረምቱ ምክንያት ባይቻልም 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ወጭ የተደረገበት 320 ሰዎችን የሚይዝ 8 ብሎክ ሼድ ተገንብቶ በሚቀጥለው ሳምንት አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ብለዋል።

የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የጥፋት ኃይሎችን ሴራ ለማምከንና ከምንጩ ለማድረቅ ሕዝቡን ያሳተፈ ጠንካራ የመንግሥት አደረጃጀትና የፖለቲካ አመራር መፍጠርና የዕለት ከዕለት ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባራችን ይሆናል ብለዋል።

በአጣዬ ከተማ በጊዜያዊ መጠለያ የተጠለሉ ተፈናቃዮችም በከተማችን አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖና በዘላቂነት ወደ ቀያችን እንድንመለስ የቤት ግንባታው ይፋጠንልን፤ የሚመጣውም የዕለት ደራሽ ምግብና ልብስ በአግባቡ ለሚመለከተው አካል ብቻ እንዲደርስ አስፈላጊው ክትትል ሊደረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። መረጃው የሰሜን ሸዋ ዞን ኮምዩኒኬሽን ነው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here